በአትሌቲክሱ የተገኘው ድል የኢትዮጵያውያንን አንድነት የበለጠ ያጠናከረ ታሪካዊ ድል ነው – አቶ ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) በአትሌቲክሱ የተገኘው ድል የኢትዮጵያውያንን አንድነት የበለጠ ያጠናከረ ታሪካዊ ድል ነው ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ፥ በአሜሪካ ኦሪገን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተመዘገበውን አኩሪ ድል በማስመልከት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም ፥ ድሉ በተለይም በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያውያንን አንድነት የበለጠ ያጠናከረ በመሆኑ ታሪካዊ ያደርገዋል ብለዋል።
ድሉ በህብረት፣ በመተጋገዝና በመተባበር ከተሰራ በአስቸጋሪ ወቅትም ቢሆን ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ያመላከተ መሆኑን ነው የገለፁት።
በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተመዘገበው አኩሪ ድልም በሌሎች ተግባራት ላይ ለመድገም መነሳሳታን የሚፈጥር ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡
በመሆኑ መላው የክልሉ ነዋሪ ብሎም አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ በሀገሪቱ እየተከናወኑ በሚገኙ የሰላምና የልማት ስራዎች በትብብር፣ በመተጋገዝና በመደጋገፍ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
ለተገኘው ውጤትም ጀግኖች አትሌቶችን፣ አሰልጣኞችንና መላው የልዑካን በድኑ አባላትን በክልሉ መንግስትና ህዝብ ስም ምስጋና ማቅረባቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡