Fana: At a Speed of Life!

በሶማሌ ክልል በኩል ሰርጎ የገባው አሸባሪው አልሸባብ ስጋት በማይሆንበት ደረጃ ተደምስሷል – አቶ ሙስጠፌ መሀመድ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቅ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በኩል ሰርጎ የገባው የአልሸባብ የሽብር ቡድን ስጋት በማይሆንበት ደረጃ በፀጥታ ኃይሎች መደምሰሱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ መሀመድ አስታወቁ፡፡

የኢትዮጵያ ጠላቶች በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍልና በምዕራብ ኢትዮጵያ የተወሰደውን የህግ ማስከበር እርምጃ ተከትሎ ሰላም የሰፈነ ሲመስላቸው ሰሞኑን በምስራቅ ኢትዮጵያ ለማጥቃት ያደረጉትን ሙከራ መክሸፉን የሀገር መከላከያ አረጋግጧል።

ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ እንዳሉት÷የአልሸባብ የሽብር ቡድን በሶማሌ ክልል ጠረፋማ አካባቢዎች ጥቃት ለመሰንዘር ሞክሯል።

ሆኖም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ጋር ባካሄደው ኦፕሬሽን የሽብር ቡድኑ ሴራ ሙሉ ለሙሉ መክሸፉን ነው የገለጹት።

ቡድኑ በክልሉ ነዳጅ በሚገኘበት አካባቢ ለመንቀሳቀስ መሞከሩን ጠቅሰው÷በአፍዴር ዞን በኩል ወደ መሀል ሀገር ለመግባት ያደረገው ሙከራ ባለበት መቀጨቱን አስረድተዋል።

የሽብር ቡድኑ እንቅስቃሴ ስብጥር ካሁን ቀደሙ የተለየ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ÷ በሀገሪቱ ውስጥ ሙጃሂዲን የተባለ የሸኔ እና አልሸባብ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን የማሸበር ተልዕኮ ተሰጥቶት የተላከ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሰርጎ የገባው የሽብር ቡድኑ በሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ ስጋት በማይሆንበት ደረጃ ሙሉ በመሉ መደምሰሱን አስታውቀዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ ሴራ በተወሰደበት እርምጃ ቢከሽፍም መዘናጋት አይገባም እና ቡድኑ ዳግም ሰርጎ እንዳይገባ ለማድረግ የፀጥታ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት ከፌዴራል የፀጥታ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ እንደሚገኝ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በማህበራዊ የትስስር ገፆች በሰሜኑ የህልውና ዘመቻ ወቅት እንደተደረገው ሁሉ ኪሳራ የደረሰበት የሽብር ቡድኑ ከሀገር ውስጥ ወንበዴዎች ጋር ግንባር ፈጥሮ ከፍተኛ የፀጥታ ችግር እንደተፈጠረ በማስመሰል ሽብር እየነዛ እንደሆነ መረዳት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የሀገር መከላከያ ኃይል ስምሪት ኃላፊና ጊዜያዊ የፀጥታ ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው በቅርቡ እንደገለጹት÷የኢትዮጵያ ጠላቶች በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍልና በምዕራብ ኢትዮጵያ የተወሰደውን የህግ ማስከበር ተከትሎ ሰላም የሰፈነ ሲመስላቸው ሰሞኑን በምስራቅ ኢትዮጵያ የማጥቃት ሙከራ አደርገዋል።

የአልሽባብ አሸባሪ ቡድን በሶማሌ ክልል በአምስት ትናንሽ የጠረፍ አካባቢዎች ለማጥቃት ቢሞክርም በጸጥታ ኃይሉ ሙሉ በሙሉ መክሸፉን ማስታወቃቸው ይታወሳል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.