የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ለ2015 በጀት አመት ከ5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አፀደቀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)ለሁለት ቀናት መደበኛ ጉባኤውን ያካሄደው የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ለ2015 በጀት አመት 5 ቢሊየን 138 ሚሊየን ብር በጀት በማፅደቅ ተጠናቀቀ።
ምክር ቤቱ በ1ኛ አመት 3ኛ መደበኛ ጉባኤው የድሬዳዋ መተዳደሪያ ቻርተር ለማሻሻል በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይም ተወያይቷል።
የፀደቀው የዘንድሮ በጀት ከአምናው ጋር ሲነፃፀር በ907 ሚሊየን ብር ወይም በ21በመቶ ጭማሪ አለው ተብሏል።
ከተመደበው በጀት ውስጥ 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር የህዝብን መሠረታዊ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለሚያቃልሉ ነባር የካፒታል ፕሮጀክቶች የተመደበ መሆኑ ተመልክቷል።
ከታቀደው በጀት ውስጥ 1 ቢሊየን 936 ሚሊየን ብሩ የፌደራል መንግስት ድጎማ ሲሆን፥ 561 ነጥብ 1ሚሊየን ብር በጀት ደግሞ ከልማት አጋር አካላት ለአስተዳደሩ ፈሰስ የሚደረግ መሆኑን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።