የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ የአፍሪካ ስመጥር ዋና ስራ አስፈጻሚዎች ሽልማትን አሸነፉ
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በቴሌኮሚኒኬሽን ዘርፍ የ2022 የአፍሪካ ስመጥር ዋና ስራ አስፈጻሚዎች ሽልማትን አሸንፈዋል፡፡
ሽልማቱ የተበረከተላቸው ዘ ቢዝነስ ኤግዚኪዩቲቭ የተሰኘ በጋና የሚገኝ የፓን ዌስት አፍሪካ ሚዲያ በሞሪሽየስ ባዘጋጀው የ2022 የአፍሪካ ስመጥር ዋና ስራ አስፈጻሚዎች ሽልማት ስነ-ስርዓት ላይ መሆኑን ከኢትዮ ቴሌኮም ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የሚዲያ ተቋሙ በአፍሪካ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ዋና ስራ አስፈጻሚዎችን ለ17ቱ የተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግቦች በአፍሪካ ለሚኖረው ስኬት ላደረጉት አስተዋጽኦ በየዘርፋቸው አወዳድሮ መሸለሙ ተገልጿል፡፡
በቴሌኮሚዩኒኬሽን ዘርፍ የሞሮኮው ማሮክ ቴሌኮም፣ የኬንያው ሳፋሪኮም ፣ የግብጹ ኢትሳላት እንዲሁም የኢትዮጵያው ኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚዎች ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው መቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡
በውድድሩም የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ የ2022 የአፍሪካ ስመጥር ዋና ስራ አስፈጻሚዎች ሽልማት ተሸላሚ መሆናቸውን የሚዲያ ተቋሙ አስታውቋል፡፡