ቻይና ለመጀመሪያ ጊዜ የሰራችው ሲ-919 የመንገደኞች አውሮፕላን የሙከራ በረራውን አጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቻይና ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራው ለንግድ አገልግሎት የሚውል ሲ-919 ትልቅ የመንገደኞች አውሮፕላን የሙከራ በረራውን ማጠናቀቁን የቻይና የንግድ አውሮፕላኖች ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
ኩባንያው አውሮፕላን የማምረት ሥራውን በ2015 አቋርጦ የነበረ መሆኑን ያሰታወሰው ዘገባው፥ በ2017 የተሳካ የመጀመሪያ በረራውን ማድረጉን ገልጿል።
ከ2019 ጀምሮ ስድስት ሲ-919 ጄቶችን በማምረት ሻንጋይን ጨምሮ የተለያዩ የምድርና እና የአየር በረራ ሙከራዎች መደረጋቸውም ተጠቅሷል።
እ.ኤ.አ. በህዳር 2020፣ ሲ-919 የፍተሻ ፍቃድ ከማግኘቱም በላይ፥ ስድስት የሲ-919 አውሮፕላኖች የሙከራ በረራቸውን በሐምሌ 19 ማጠናቀቃቸውን ነው ኮማክ የገለጸው።
የምሥራቅ አየር መንገድ፥ አውሮፕላኑ ሻንጋይን ከሌሎች ዋና ዋና ከተሞች ጋር በሚያገናኙት የሀገር ውስጥ በረራዎች ላይ ለማሰማራት ማቀዱንም አስታውቋል።
በዚህም መሰረት አውሮፕላኑ በሚያደርገው የአገር ውስጥ በረራ፥ የሻንጋይ ከተማን ከቤጂንግ፣ ጉዋንግዞ፣ ሸንጀን፣ ቻንግዱ፥ ዥያመን፣ ውሃን እና ችንግዳኦ ከመሳሰሉ የአገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች እንደሚያገናኝ ተገልጿል።
በዓለም ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉት የሲቪል አቪዬሽን ኩባንያዎች መካከል ቻይና የራሷን ሲ-919 አውሮፕላን በማምረት ከዓለም አቀፍ ግዙፍ የመንገደኞች አውሮፕላን አምራቾች ከኤርባስ እና ቦይንግ ኩባንያዎች ጋር እየተፎካከረች እንደምትገኝ የሲጂቲኤን ዘገባ አመላክቷል፡፡