ሀገርና ሕዝብን በማስቀደም የተጀመሩ የሰላም አማራጮችን ውጤታማነት ማረጋገጥ ይገባል – የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገርና ሕዝብን በማስቀደም የተጀመሩ የሰላም አማራጮችን ውጤታማነት ማረጋገጥ ይገባል አሉ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን በሰጡት አስተያየት ፥ የሀገራዊ ምክክሩ ሂደትና በመንግሥት የተጀመረው ለሰላም አማራጭ ቅድሚያ የመስጠት ውሳኔ አዲስ ምዕራፍ ከፋች ናቸው ብለዋል፡፡
ድህረ ግጭት በበርካታ ሀገራት ሰላምን ለማስፈን ድርድሮች ወሳኝነት እንደነበራቸው በማንሳት ለውጤታማነቱ የሁሉም ወገኖች በጎ ዕይታና ይሁንታ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ዶክተር ደጉ አስረስ ፥ ከግጭት የሚገኘው ውድመትና ጉዳት በመሆኑ ለሰላም አማራጮች ማመንታት አያስፈልግም ሲሉ መክረዋል፡፡
መንግሥት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እያሳየ ያለው ሆደ ሰፊነት በአወንታዊነት የሚነሳ ነው ያሉት በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ የአፍሪካ ጥናት መምህሩ ንጋቱ አበበ ፥ ሌሎች ወገኖችም ልዩነታቸውን ወደ ጠረጴዛ ማምጣት አለባቸው ብለዋል፡፡
ሀገራዊ ምክክሩንና ሰላማዊ ውይይቶችን “ለአገራችን ወርቃማ እድል ናቸው “ ያሉት ምሁራኑ ፥ ዕድሉን አባክነው የታሪክ ተወቃሽ ላለመሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
ለሰላም የሚያስፈልገው ወጪ ለጦርነት ከወጣው ያነሰ ነው ያሉት ምሁራኑ፥ ሁሉም ለሰላም የሚከፈልን ዋጋ ለማበርከት ዝግጁ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
ያኮረፉ ቡድኖችም መፍትሄው ሰላማዊ ንግግር መሆኑን በመገንዘብ ለሰላማዊ ውይይትና ድርድር ራሳቸውን ማዘጋጀት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
በአፈወርቅ እያዩ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!