ለሕግ ታራሚዎች ተገቢውን አያያዝ እና የፍትሕ አገልግሎት ማቅረብ እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕግ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ተገቢው አያያዝ ማግኘት እንዳለባቸው እና በቆይታቸውም ፍትሕ አግኝተው ታንጸው እንዲወጡ መሥራት እንደሚገባ የፍትሕ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ገለጹ፡፡
ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ÷ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ማረሚያ ቤት ተገኝተው የታራሚዎችን አያያዝ ጎብኝተዋል፡፡
በማረሚያ ቤቱ በነበራቸው ቆይታም የሕግ ታራሚዎች ፍትሃዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻል እንደሚገባ አጽንት ሰጥተዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጠቅላይ ዓቃቢ ሕግ ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ አማር ረጅብ በበኩላቸው ÷በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው በህግ ጥላ ሥር የሚገኙ ታራሚዎች አያያዝና ፍትሕ አሠጣጥ ላይ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በቅርበት እየሠሩ እንደሆነ ገልጸዋል።
ታራሚዎቹ ከማረሚያ ቤት ወጥተው ወደ ማኅበረሰቡ ሲመለሱ የወንጀልን አስከፊነትና የሠላምን አስፈላጊነት ማስተማር እንዲችሉ በቆይታቸው ተገቢ የንቃተ-ሕግ ትምህርት ማግኘት እንዳለባቸው መናገራቸውን ከዞኑ ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡