አምራቾች ውጤታማነታቸውን ለማስቀጠል ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት እንደሚገባቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚሠሩ አምራቾች የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታትና ውጤታማ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሠራርን መተግበር እንደሚገባቸው ተገለጸ፡፡
በዘርፉ የሚታየውን ችግር ለመፍታትና ውጤታማነታቸውን ማስቀጠል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተካሂዷል።
የኢንዱስትሪ ሚንስትር አቶ መላኩ አለበል በውይይቱ ላይ እንደገለጹት÷ የአምራች ዘርፉ የሀገራችንን መፃኢ-ዕድል የሚወስን እና በዘርፉም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ ሁሉም የፌዴራል፣ የክልል ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሠሩ ማሳሰባቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
ሥራዎችን በቅንጅት አለመሥራት ፓርኮችን ውጤት አልባ ከማድረጉም ባለፈ የሀገርን ጥቅም የሚጎዳ በመሆኑ ቁልፍ ተግዳሮቶች እና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በመለየት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በኃላፊነት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ በኢትዮጵያ በሚገኙ 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ደረጃቸውን የጠበቁና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ሼዶች መገንባታቸውን ተናግረዋል፡፡
ሼዶቹም መሰረታዊ አገልግሎቶች ተሟልተውላቸው የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ገብተው በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ገልጸው÷ የባለሃብቶቹን ውጤታማነት ለማስቀጠልና ትርፋማነታቸውን ለማረጋገጥ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባና ሁሉም ባለድርሻ አካል የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡