Fana: At a Speed of Life!

የኦዲት ሥራን ውጤታማ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት መንፈስ እንዲሰሩ ጥሪ ቀረበ

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ሀብት እንዳይባክን ኦዲተሮች በሚያደርጉት ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት መንፈስ ለኦዲት አፈጻጸም ውጤታማነት በትጋት መስራት አንዳለባቸው የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካለኝ አሳሰቡ፡፡

የፌዴራል ዋናው ኦዲተር በ2013 በጀት ዓመት ባለበጀት መስሪያ ቤቶችን ኦዲት አድረጎ ተቀባይነት የሚያሳጣ የኦዲት አስተያየት ከተሰጣቸው የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ ዶክተር እዮብ ተካለኝ እንደገለጹት፥ የኦዲት ስራ በየመስሪያ ቤቱ የተዘረጋው የቁጥጥር ስርዓት ውጤታማ አንዲሆን በጥብቅ ስልትና ስርዓት ተመርቶ የህዝብ ሃብት ከብክነት እንዲድንና ተቋማት የተመሰረቱበት ዓላማ ግቡን እንዲመታ ሁሉም በባለቤትነት መንፈስ ሊሰራ ይገባል፡፡

መንግሥት የኦዲት ስራ ውጤታማ አንዲሆን መዋቅራዊ ችግሮችን ለመፍታትና የውስጥ ኦዲተሮችንም ሆነ የዋና ኦዲተር ኦዲተሮችን ችግሮች ለመፍታት እንዲሁም የአቅም ክፍተታቸውን ለመሙላት ዝግጁ መሆኑን ጠቁመው፥ የስነምግባር ችግር ያለባቸውን ኦዲተሮች ግን በፍጹም እንደማይታገስና የማያዳግም እርመጃ እንደሚውስድ አሳስበዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ጄኔራል ወይዘሮ መሰረት ዳምጠው ፥ የኦዲት ስራ ዋንኛ አላማ የኦዲት ግኝት ተስተካክሎ ለስራ የተመደበው በጀት በአግበቡ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ማስቻል መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ኦዲተሮችና ኦዲት ተደራጊ መስሪያ ቤቶች ለጋራ ዓላማ ተባበረው መስራት እንዳለባቸው ገልጸው ፥ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ ማቅረባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገነኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ በምክክር መድረኩ የተገኙትና ተቀባይነት የሚያሳጣ የኦዲት አስተያት የተሰጣቸው የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ሃላፊዎችና የፋይናንስ ባለሙያዎች በኦዲት ሂደቱ የተከሰቱ ችግሮችን ማለትም የኦዲተሮች አቅም ማነስ፣ የስነምግባር ችግር፣ ከኦዲት ተደራጊ ተቋማት የሚፈለገውን ግዴታ በግልጽ ያለማሳወቅና ሌሎች በርካታ ችግሮችን አንስተው መፍትሄ እንዲፈለግላቸው ጠይቀዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.