ኢትዮጵያ በቻይና ገበያ ያላትን ድርሻ ከፍ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ተባለ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በቻይና የኦንላይን ግብይት መድረኮች ላይ የምታቀርባቸውን የምርት አይነቶች በመጨመር በገበያው ያላትን ድርሻ ከፍ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ሲሉ በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን መሪ አምባሳደር ዳዋኖ ከድር ገለጹ፡፡
ሚሲዮኑ ከሐምሌ 27 እስከ ዛሬ የጄጂያንግ ክፍለ ሀገር ርዕሰ መዲና በሆነችው የሀንጆ ከተማ በተካሄደው ዘጠነኛው የቻይና ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ ግብይት አውደርዕይ ላይ ተሳትፏል።
የሚሲዮኑ ምክትል መሪ አምባሳደር ዳዋኖ ከድር በአውደርዕዩ የመክፍቻ መርሐ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ፥ ኢትዮጵያ በቻይና የበይነ መረብ ግብይት መድረኮች ላይ የምታቀርባቸውን የምርት አይነቶች በመጨመር በገበያው ያላትን ድርሻ ከፍ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዘርፉ የተሰማሩና ልምድ ያካበቱ የቻይና ኩባንያዎች የኢትዮጵያ የውጭ ሽያጭ ምርቶች በቻይና የበይነ መረብ መገበያያ መድረኮች ላይ በስፋት እንዲገቡ ለማድረግ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በአውደርዕዩ ቡናን ጨምሮ ለውጭ ሽያጭ የሚቀርቡ የተለያዩ የኢትዮጵያ ምርቶች ለእይታ ቀርበው በተሳታፊዎች መጎብኘታቸውን በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ከአውደርዕዩ ጎን ለጎንም አምባሳደር ዳዋኖ ከሀንጆ ከተማ ምክትል ከንቲባ፣ ከጄጂያንግ ውጭ ጉዳይ ቢሮና ከጂጂያንግ – አፍሪካ የንግድ አገልግሎት ማዕከል ሃላፊዎች እንዲሁም ከአሊባባ ኩባንያ ተወካዮች ጋር በበይነ መረብ ንግዱ ዘርፍ ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር በሚያስችሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።