4ኛው ዙር የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ስልጠና ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጅማ ዩንቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት ለብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ ልማት አገልግሎት ሰልጣኞች ሲሰጥ ነበረው ስልጠና ተጠናቋል፡፡
በ4ተኛው ዙር ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ ልማት አገልግሎት ፕሮግራም በጎነት ለአብሮነት በሚል መሪ በተለያዩ ዩኒቨርሰቲዎች ከ 9 ሺህ በላይ ወጣቶች ስልጠናቸውን ጨርሰው የተመረቁ ሲሆን÷ በዛሬው ዕለት በጅማ ዩኒቨርሲቲ ከ1ሺህ 500 በላይ ሰልጣኞች ተመርቀዋል፡፡
የሰላም ሚኒስትር አማካሪ አምባሳደር እሸቴ ደሴ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የብሔር መከፋፈልና ግጭቶችን ለማስቀረት በበጎነት ለአብሮነት ማዕቀፍ ውስጥ የሚሰጠው ስልጠና በባህል ልውውጥና እርስ በመማማር የሀገሪቱ እሴቶች ላይ መሰረት ያደረገ በመሆኑ ለሰላም ግንባታ የማይተካ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡
በበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ሥራ ላይ መሳተፍ ዕድለኝነት፣ የህሊናና የመንፈስ እርካታ የሚሰጥ ተግባር መሆኑን በመገንዘብ÷ በዘላቂ ሰላምና ሀገራዊ መግባበት ሥራ ውስጥ የራሳችሁን ዐሻራ ልታሳርፉ ይገባል ብለዋል፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል አባፊጣ÷ ከእናንተ ብዙ የሚማሩ በብዙ የሚያተርፉ በርካቶች ናቸውና ከሰውነት ሳትጎድሉ ሀገራችሁ የሰጠቻችሁን ኃላፊነት እና የዜግነት ግዴታችሁን በሙሉ ኢትዮጵያዊ ልብ ልትተገብሩ ይገባል ማለታቸውን የሰላም ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!