በመዲናዋ ለህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የተደረገውን የነዳጅ ድጎማ የሚቆጣጠር ግብረ ኃይል ተቋቋመ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ተግባራዊ የተደረገው የነዳጅ ድጎማ ያለምንም መስተጓጎል፣ በውጤታማነትና በዘላቂነት የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ ለማድረግ የሚያስችል ግብረ ሃይል ተቋቋመ።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ በተገኙበት በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ በትራንስፖርት አገልግሎት የሚያጋጥመውን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለማቃለል መንግሥት ለብዙሃን ትራንስፖርት ዘርፍ ያደረገው የነዳጅ ድጎማ ያለፈው አንድ ወር የትግበራ ሂደት ያለበት ደረጃና አፈፃፀም ተገምግሟል።
በዚሁ ወቅት የነዳጅ ድጎማው ተግባራዊ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ባለው የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የታለመ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ የሚሆኑ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች መረጃ መደራጀቱ፣ በቴክኖሎጅ በታገዘ አግባብ ምዝገባ መደረጉ፣ አብዛኞቹ በነዳጅ ማደያዎች በኩል በቴሌ ብር ግብይት እያካሄዱ መሆናቸው በጥንካሬ የሚወሰድ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተመላክቷል ።
ከዚህ ጎን ለጎን ለህዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች እየተደረገ ያለው የነዳጅ ድጎማ በታለመው ልክ ውጤታማ እንዲሆን በአፈፃፀም ሂደቱ የታዩ ክፍተቶች በፍጥነት እንዲስተካከሉ አቶ ጥራቱ በየነ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በተለይም ያልተመዘገቡ ቀሪ የህዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ምዝገባ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ፣ ተመዝግበው በቴሌ ብር መጠቀም ያልጀመሩ እንዲጀምሩ፣ በድጎማ መሰረት በወጣው ታሪፍ ብቻ አገልግሎት እንዲሰጥና ይህን ተግባራዊ በማያደርጉት ላይ ህግና ስርዓቱን ተከትሎ ቁጥጥር እንዲደረግ አሳስበዋል።
በከተማው ለህዝብ ትራንስፖርት ሰጪ ተሽከርካሪዎች የሚደረገው የነዳጅ ድጎማ ውጤታማ እንዲሆን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ግብረ ሃይል መቋቋሙን ከከተማው ከንቲባ ጽኅፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የተቋቋመው ግብረ ሃይል አባላት ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ፣ ከትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ባለስልጣን፣ ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ፣ ከከንቲባ ፅህፈት ቤትና ከቴሌኮሙኒኬሽን የተውጣጡ ናቸው።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!