በኦሮሚያ ክልል እስካሁን 5 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዚህ ዓመት የክረምት ወራት የእርሻ ልማት መርሐ ግብር እስካሁን 5 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን መቻሉ ተገልጿል፡፡
በዚህ ዓመት የክረምት ወቅት በአጠቃላይ በክልሉ የሚገኘውን 6 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር ያህል የእርሻ መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ ሲሆን፥ እስካሁን ድረስ 5 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር ያህሉን መሬት በዘር መሸፈን መቻሉን የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ አበራ ወርቁ መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በክልሉ በዘር ለመሸፈን ከታቀደው የእርሻ መሬት ውስጥ 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር ያህሉ ላይ ስንዴ ለመዝራት የታቀደ ሲሆን፥ እስካሁን በ1 ነጥብ 3 ሚሊየን ያህል ሄክታር ላይ ስንዴ ተዘርቶ መጠናቀቁም ነው የተመለከተው፡፡