Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና በመከረው ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ ተሳተፈች

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 17 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያበመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ልማት ጉባዔ ላይ ተሳተፈች።

ጉባዔው “የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ልማት ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ አዲስ ለውጥ፤ አዲስ መንገድ እና አዲስ ክኅሎት” በሚል መሪ ቃል በቻይና ቲያንጂን ተካሂዷል።

የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ባስተላለፉት መልዕክት የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ከሀገሪቱ ማኅበረ ኢኮኖሚ ዕድገት ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል።

አያይዘውም ቴክኒክና ሙያ ትምህርት የሥራ ዕድል ፈጠራን እና የህዝቦችን ኑሮ ለማሻሻል ያለውን ሚናም ጠቅሰዋል።

በጉባዔው ላይ በበይነ መረብ መልዕክት ያስተላለፉት የሥራ እና ክኅሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ለሀገሪቱ ማኅበረ-ኢኮኖሚ ዕድገት ያለውን ጠቀሜታ እንገነዘባለን ብለዋል።

አያይዘውም በፈረንጆቹ 2021 የተመሠረተው የ“ሉባን ሰርት ማሳያ ኢትዮጵያ” ከቲያንጂን ቴክኖሎጂና ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ጋር እንዲሁም ከኢትዮጵያ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በዘርፉ የልኅቀት ማዕከል በመሆን እያገለገለ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሁሉም የሰርቶ ማሳያ የሥልጠና ሞጁሎቹ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ እንደሆኑም አመላክተዋል።

የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ተሻለ በሬቻ፥ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና በኢትዮጵያ በሥራ ዕድል ፈጠራ እያበረከተ ያለውን ሚና አስረድተዋል፡፡

ኢኒስቲትዩቱ ከቲያንጂን የቴክኖሎጂ እና ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስረድተዋል።

በጉባኤው በቻይና የኢትዮጵያን ኤምባሲ በመወከል አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ከቲያንጂን ከተማ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና የሚዲያ አካላት ጋር የጎንዮሽ ውይይት አድርገዋል፡፡

700 በመንግስት የተወከሉና ሌሎች ተሳታፊዎች መገኘታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ የዓለም የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ማሰልጠኛ ሊግ የተመሰረተ ሲሆን፥ ዓለም አቀፍ የሙያ ትምህርት ሽልማት እና የቲያንጂን ኢኒሼቲቭ ፕሮፖዛልም በይፋ ተጀምረዋል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.