Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያን መንግስት የሰላም ጥረት ሀገራቸው እንደምትደግፍ የደቡብ ኮሪያ የምክር ቤት አባላት ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በመንግሥት የተጀመረውን ጥረት ደቡብ ኮሪያ እንደምትደግፍ የሀገሪቷ የምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከደቡብ ኮሪያ የምክር ቤት ልዑካን ቡድን አባላት ጋር የሁለቱን ሀገሮች ወዳጅነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ፈትሂ ማህዲ፥ ሁለቱ ሀገራት በመተባበር ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

ሀገራቱ በምጣኔ ሐብት፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በልማት እንዲሁም በሰላምና ጸጥታ ያላቸውን የቆየ የትብብርና ግንኙነትም አብራርተዋል።

የደቡብ ኮሪያ ምክር ቤት አባልና የውጭ ጉዳይ የአንድነት ኮሚቴ አባል ኪም ታኢ ሆ፥ በኢትዮጵያ መንግሥት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ስለተደረጉ ጥረቶች መረዳታቸውን ገልጸው፥ ለዚህም ሀገራቸው ድጋፍ የምታደርግ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በ1950ዎቹ በሰሜን ኮሪያና ደቡብ ኮሪያ በነበረው ጦርነት ኢትዮጵያ ወታደሮቿን በመላክ ለሰላም የነበራትን ሚና በማስታወስ የሀገራቸው ባለውለታ መሆኗን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የቡድኑ ጉብኝት አንደኛው ዓላማ የደቡብ ኮሪያ በዓለም የምግብ ፕሮግራም አማካኝነት የምትለግሰውን ሰብአዊ ዕርዳታ ተደራሽነትን በማረጋገጥ በቀጣይ ድጋፋቸውን ለማጠናከር መሆኑንም ጨምረዋል።

ደቡብ ኮሪያ በግብርና፣ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ሌሎች ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መሥራት እንደምትሻም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የውሃ ሃብቷን አልምታ ለመጠቀም የምታደርገው ጥረትም የሚደገፍ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮ-ደቡብ ኮሪያ የወዳጅነት ቡድን በምክር ቤት ደረጃ በመመስረት የሁለቱን ሀገሮች የፓርላማ የትብብር ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰራም ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢትዮ-ደቡብ ኮሪያ የወዳጅነት ቡድን በምክር ቤት በመመስረት የሁለቱን አገሮች የፓርላማ የትብብር ግንኙነት ለማጠናከር ይሰራል ተብሏል።

የኢትዮ- ደቡብ ኮሪያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1963 እንደተጀመረ መረጃዎች ያሳያሉ።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.