ደቡብ ሱዳን ለኢትዮጵያ ያላትን ጠንካራ ድጋፍ በድጋሚ አረጋገጠች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ሀገራቸው ለኢትዮጵያ ያላትን ጠንካራ ድጋፍ በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡
የመከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ ከደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንት ታባን ዴንግ እንዲሁም ከሀገሪቷ ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር የደኅንነት ጉዳዮች አማካሪ ቱት ጋትሉዋክ ጋር መክረዋል፡፡
የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በዚህ ወቅት ሀገራቸው በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ከኢትዮጵያ ጋር ለመቆም የማይናወጥ አቋም እንዳላት ተናግረዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች በቀጣናው የሠላም እና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ መምከራቸውም ነው የተመለከተው፡፡
በውይይታቸው ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን በትብብር መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ አጽንኦት መስጠታቸውን በጁባ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመላክቷል፡፡
አመራሮቹ ሀገራቱን በመሠረተ-ልማት ማስተሳሰር ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተም ተወያይተዋል ነው የተባለው፡፡
በአጭር ጊዜም ሀገራቱን ብሎም የቀጣናውን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ በመንገድ ግንባታ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሁም በነዳጅ መሠረተ-ልማት ግንባታዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡