ለበዓል አስፈላጊ ፍጆታዎች ለህብረተሰቡ እየቀረቡ ነው- የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ከበዓል ጋር ተያይዞ የዋጋ ንረት እንዳይፈጠር የተመረጡ የምግብ ፍጆታዎች ለህብረተሰቡ እየቀረቡ መሆኑን የከተማዋ ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ አደም ኑሪ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ ከመጪው የዘመን መለወጫ እና ሌሎች በዓላት ጋር ተያይዞ በምግብ ፍጆታ ሸቀጦች ላይ የአቅርቦት እጥረት እና የዋጋ ንረት እንዳይከሰት በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው፡፡
ሥራውም በአቅርቦት፣ በግብይት ቁጥጥር እና ከከተማ እስከ ወረዳ በተዘረጋ የመረጃ ልውውጥ ዘርፎች እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለህብረተሰቡ እየቀረቡ ያሉት የምግብ ፍጆታዎች የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርቶች መሆናቸውን ገልጸው÷ የአቅርቦት እጥረት እንዳይኖርም ከክልል ኅብረት ሥራ ዩኒየኖች እና ከፋብሪካዎች ጋር በቅርበት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ለህብረተሰቡ እየቀረቡ ያሉት ምርቶችም÷ ዘይት፣ ዱቄት እና ስኳር እንዲሁም ጤፍ፣ ሽንኩርት፣ የእርድ ከብት፣ ዶሮ፣ እንቁላል፣ ዓይብ እና ቅቤ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
ምርቶቹ በተለያዩ አማራጮች ተደራሽ እንደሚሆኑ ጠቅሰው÷ ጤፍ፣ ስኳር እና ዘይት በመዲናዋ በሚገኙ 148 የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ንብረት በሆኑ 862 ሱቆች እንደሚገኙም አመላክተዋል።
እንዲሁም የእነዚሁ ማኅበራት ንብረት በሆኑ 240 የልኳንዳ ቤቶች÷ በቅርጫም ሆነ በኪሎ ሥጋ መሸመት ለሚሹ ወገኖች 1 ኪሎ ስጋ ከ300 እስከ 360 ብር እንደሚሸጥ ተናግረዋል፡፡
ሦስተኛው የአቅርቦት ማግኛ አማራጭ የገበያ ማዕከላት መሆናቸውን ጠቁመው÷ እንደከተማ በቋሚነት አራት የቁም እንስሳት መሸጫ ማዕከላት (አቃቂ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል አካባቢ፣ ቄራ፣ ካራሎ ወሰን አካባቢ እና ጉለሌ ሸጎሌ አካባቢ) መኖራቸውንም ነው የገለጹት።
በጊዜያዊነት ደግሞ በዓሉ ሲቃረብ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከፈቱ የገበያ ማዕከላት ይኖራሉም ነው ያሉት።
በዓላትን በማስታከክ የአቅርቦት እጥረት እና የዋጋ ንረት እንዳይከሰትም አምራች እና ሸማችን በስፋት ማገናኘት ላይ በትኩረት መሥራት ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ለዚህም አምራች እና ሸማች ገበያ እንዲያገኙ በመሀል ያለን የደላላ ሰንሰለት ማሳጠር ሁነኛ መፍትሔ ነው ብለዋል፤ ለዚህም “እንደ እሁድ ገበያ” ያሉ ተሞክሮዎችን ማስፋት እንደሚገባ በመጥቀስ።
በመሠረታዊነት የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍ የምርት እና የመግዛት አቅም ማደግ ወሳኝ ጉዳይ ስለሆነ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የሚሰራ መሆኑንም አመላክተዋል።
በዮሐንስ ደርበው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!