የመውጫ ፈተና ለግልና ለመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የጋራ መመዘኛ ነው – የትምህርት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመውጫ ፈተና ለግልና ለመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የጋራ መመዘኛ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ገለፀ፡፡
ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመውጫ ፈተና ዙሪያ ውይይት ተደርጓል ፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ፥ የመውጫ ፈተና የሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዱና ዋነኛው የጋራ መወዳደሪያ መስፈርት ነው፡፡
የመውጫ ፈተናን ውጤት መሰረት በማድረግም የግልና የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እርስ በርሳቸው እንደሚወዳደሩ ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተዋል፡፡
በመሆኑም ጥሩ ውጤት ሊገኝ የሚችለው ጥሩ ሂደት ሲኖር በመሆኑ ተቋማቱ ተማሪዎች ለውጤት እንዲበቁ ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡
የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ኤባ ሚጀና በበኩላቸው ፥ በመውጫ ፈተና ዝግጅትና አስተዳደሩ ላይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉበትና በትምህርት ሚኒስቴር አስተባባሪነት በማእከል እንደሚዘጋጅ ገልጸዋል፡፡
ተማሪዎች ለምረቃ መብቃትና የትምህርት ማስረጃዎቻቸውንም መውሰድ የሚችሉት የመውጫ ፈተናውን ካለፉ በኋለ መሆኑን ጠቁመው ፥ በፈተናው ያላለፉ ተማሪዎችም ተገቢውን ዝግጅት በማድረግ ደግመው መፈተን የሚችሉበት አሰራር እንደሚኖር አስታውቀዋል፡፡
የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመውጫ ፈተና ዙሪያ ለሚያደርጉት ዝግጅትም የትምህርት ሚኒስቴር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚው አረጋግጠዋል፡፡
የግል ከፍተኛ ትምህርት እና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ሞላ ጸጋዬ ፥ በ3ኛ ዲግሪ እየተሰጠ ያለው የትምህርት እድል ከፍ እንዲል መጠየቃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በግልና በመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚታዩ የህግ አተገባበር ልዩነቶች እንዳሉ ጠቅሰው ፥ እንዲስተካከል ጠይቀዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!