በዓመት 10 ሺህ ትራክተሮችን ማምረት የሚያስችል ፋብሪካ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሞጆ ከተማ በዓመት 10 ሺህ ትራክተሮችን ማምረት የሚያስችል ፋብሪካ ለመገንባት በዛሬው ዕለት የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡
ፋብሪካውን የሚገነባው በቻይና ቁጥር አንድ የትራክተር አምራች ዋይቲኦ-ሲኤኤምኤሲኦ የተሰኘው ኩባንያ ሲሆን÷በ2015 የበጀት ዓመት ግንባታውን አጠናቆ ስራ ለማስጀመር እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመሩ ተመላክቷል፡፡
የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚው አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷የአዳማ ግብርና ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ በመሆኑ ዘመኑ የደረሰበት የግብርና ማምረቻ ፋብሪካ መገንባት ማስፈለጉን ጠቁመዋል፡፡
በአፍሪካ የመጀመሪያ የሚሆነው ይህ ፋብሪካ÷በቀን 50 ትራክተሮችንና በዓመት ከ10 ሺህ በላይ ትራክተሮችን የሚያመርት በመሆኑ ለሀገራችን ግብርና የጀርባ አጥንት መሆኑን አምባሳደር ምስጋኑ ተናግረዋል።
በየክልሉ የሰርቪስ ማዕከላት ለመገንባትና በቀጣይ መገጣጠሚያ ለማድረግ መታቀዱም ነው የተገለጸው፡፡
የዋይ ቲ ኦ ዓለም አቀፍ ዳይሬክተር ሚስተር ሊዩ ፒ በበኩላቸው÷ ኩባንያው የቻይናን ግብርና ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዘመናዊ የቀየረ በመሆኑ የኢትዮጵያን የግብርና ዘርፍ ለማዘመን ከኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አብረሃም በላይ÷ የለውጡ መንግስት የመጀመሪያ ትኩረት ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕን በአዲስ አስተሳሰብ እንዲመራ ማድረግ እንደሆነ አስታውሰዋል።
ከግዥና ችርቻሮ ወጥቶ በአምራችነት እንዲሠማራ ማድረግ በመሆኑ የዛሬው ፕሮጀክትም ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው ማለታቸውን ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡