ህብረተሰቡ በዓላትን ሲያከብር እራሱን ከአደጋ እንዲጠብቅ ኮሚሽኑ አሳሰበ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ህብረተሰቡ የዘመን መለወጫን ጨምሮ ሌሎች በዓላትን ሲያከብር እራሱን ከአደጋ እንዲጠብቅ የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፍስሐ ጋረደው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ÷ ህብረተሰቡ ከበዓል ጋር በተያያዘ በተለይም ምግብ ሲያበስል ጥንቃቄ በጎደለው የማገዶ እንጨት፣ ከሰል እና ኤሌክትሪክ አጠቃቀም ምክንያት የቃጠሎ አደጋ ሊከሰት ይችላል ብለዋል፡፡
ስለሆነም ህብረተሰቡ እነዚህን የኃይል ምንጮች ከመጠቀሙ በፊት እና ከተጠቀመ በኋላም ለአደጋ መንስኤ የሚሆኑ ጉዳዮች አለመኖራቸውን ሊያረጋግጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ምግብ አብስለው ከጨረሱ በኋላም ሁሉም የኃይል ምንጮች (የማገዶ እንጨት፣ ከሰል እና ኤሌክትሪክ) አደጋ በማያስከትሉበት ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ኮሚሽኑ አደጋ በመቀነስ እና በአደጋ ምላሽ ዘርፍ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁንም ኮሚሽነር ፍስሐ ገልጸዋል፡፡
አደጋ ከመፈጠሩ በፊት በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ግንዛቤ በመፍጠር እና አደጋ ቢከሰት ደግሞ በመዲናዋ በሚገኙ በዘጠኝ ዋና ዋና ቅርንጫፎች እንዲሁም በሥራቸው በሚገኙ ንዑስ ቅርንጫፎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል፡፡
አደጋ የሌለበት እና ሰላማዊ በዓል እንዲሆን ህብረተሰቡ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ የራሱን ኃላፊነት እንዲወጣ ኮሚሽነር ፍስሐ ጠይቀዋል፡፡
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ በበኩላቸው÷ ከምግብ ማብሰል ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ አደጋዎች አብዛኞቹ በድካም እና ባለማስተዋል እንደሚፈጠሩ ጠቁመው የቤተሰብ አባላት የበዓል ሥራን ተከፋፍለው ቢሠሩ ይመከራል ብለዋል፡፡
እንዲሁም ከከሰል አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸው÷ ሰሞኑን ከዚህ ጋር በተያያዘ የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን አስታውሰዋል፡፡
ድንገተኛ አደጋ ከተፈጠረም በ939 ነጻ የስልክ መስመር ወይም 011 155 53 00ን እንዲጠቁም ጠይቀዋል።
በዮሐንስ ደርበው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!