የጤና ሚኒስቴር ያሰባሰበውን የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስረከበ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማትና ሠራተኞቹ ያሰባሰበውን የትምህርት ቁሳቁስ ለአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስረከበ።
ድጋፉን ያስረከቡት የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ÷ ይህኛው ድጋፍ የበፊቶቹ ጊዜያትድጋፎች አንዱ አካል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዓላማውም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወላጆችን ካለባቸው ጫና ማሳረፍ ነው ብለዋል ።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተሰጠው ዋነኛ ተልዕኮ በተጨማሪ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ እየተሳተፈ እንደሚገኝም ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡
ከ 1 ሚሊየን በላይ ዜጎች በጤና ሚኒስቴር የነፃ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉንም ነው የጠቆሙት፡፡
ባለፉት ዓመታት በሥፋት ሲተገበር በቆየው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ÷ የጤና ሚኒስቴርም በአዲስ አበባ እና በጋምቤላ ክልል የአቅመ ደካማ አረጋውያንን ቤት በማደስ እንደተሳተፈም ገልጸዋል።
ድጋፉ ለ900 ተማሪዎች የሚከፋፈል ሲሆን በወቅቱ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አድማሱ ደቻሳ ተቀብለዋል፡፡