በአዲሱ አመት በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በትኩረት ይሠራል – አቶ ኡሞድ ኡጁሉ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ያለው ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረው በአዲሱ ዓመት የክልሉ መንግሥት በትኩረት ይሠራል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ገለፁ።
አቶ ኡሞድ አዲሱን ዓመት በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ባስላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት÷ በመጠናቀቅ ላይ ባለው 2014 ዓ.ም በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ሆነን በርካታ ስኬቶችን አስመዝግበናል ብለዋል።
በጋምቤላ ከተማ አጋጥሞ የነበረውን የፀጥታ ችግር በተቀናጀ መንገድ ከመመከት ባለፈ በአሁኑ ሰዓት በክልሉ አንጻራዊ ሰላም መኖሩን አንስተዋል፡፡
በ2014 ዓ.ም የተከናወኑ ውጤታማ ሥራዎችን ማጠናከርና የተስተዋሉ ውስንነቶችን መቅረፍ እንዲሁም ያጋጠሙ ፈተናዎችን ለማለፍ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
በክልሉ በጎርፍ አደጋ ምክንያት ከ187 ሺህ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን ጠቁመው÷ በቀጣይ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ማቋቋም የክልሉ መንግሥት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አንስተዋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት በኢትዮጵያውያን ላይ የከፈተውን ጦርነት በጋራ መቀልበስ እንደሚገባ ጠቅሰው÷ የክልሉ ሕዝብና መንግሥት ለመከላያ ሠራዊትና ለፀጥታ አካላት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡