አንድነታችንን በማጠናከር ህወሓት የከፈተውን ጦርነት መመከት እና ሀገርን ማጽናት ያስፈልጋል ÷አቶ አርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አንድነታችንን ይበልጥ በማጠናከር ህወሓት የከፈተውን ጦርነት መመከት እና ሀገርን ማጽናት ያስፈልጋል ሲሉ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ኦርዲን በድሪ ገለጹ፡፡
በሀረሪ ክልል የአንድነት ቀን “ስናብር ስናምር” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
በአከባበር መርሐ ግብሩ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ÷ ኢትዮጵያውያን የአንድነትን አስፈላጊነት በሚገባ የተገነዘብን ህዝቦች ነን ብለዋል፡፡
ይህን ለዘመናት የዳበረ አንድነት የበለጠ በማጠናከር በህወሓት እና በግብረ-አብሮቹ የተከፈተውን ጦርነት መመከት እና ሀገርን ማጽናት እንደሚያስፈግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በተጨማሪም የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የባህልና የማንነት ልዩነቶችን እንደ ብሄራዊ ውበት በመውሰድ የአንድነታችን የጥንካሬ ምንጭ ማድረግ እንደሚገባ ነው ያወሱት።
ለመከላከያ ሰራዊት ተገቢውን ድጋፍና ክብር መስጠት ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ የክልሉ መንግስትም ለሰራዊቱ እያደረገ የሚገኘውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡