Fana: At a Speed of Life!

በአንድነት ስንቆም የውስጥና የውጭ ጠላቶችን ድል አድርገን ህልውናችንን እናስከብራለን – አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአንድነት ስንቆም የውስጥና የውጭ ጠላቶችን ድል አድርገን ህልውናችንን እናጸናለን ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ፡፡

በጋምቤላ ክልል የአንድነት ቀን “ስናብር ስናምር” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ÷ በአንድነት ስንቆም የውስጥና የውጭ ጠላቶችን ድል አድርገን ህልውናችን እናፀናለን ብለዋል።

ሀገር የማፍረስ ተልዕኮን ያነገበው አሸባሪው ህወሓት በሀገራችን ላይ የሰነዘረውን ወረራ ለመመከት የክልላችን ህዝቦች ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ በመሆን ከፍተኛ ሚና መጫወት እንደቻሉ ነው የገለጹት።

የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን ሰላም በአንድነትና በህብረት የምናጸናበት እንዲሆን ሁሉም ዜጋ በትብብርና በአንድነት መቆም እንደሚኖርበት ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

ኅብረተሰቡ አብሮነቱንና አንድነቱን በማጠናከር በአዲሱ ዓመት ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት በትብብር ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ባንቻየሁ ድንገታ በበኩላቸው÷ በክልሉ በ2014 ዓ.ም የገጠሙንን ፈተናዎች ህብረተሰቡን በማሳተፍ እየፈታናቸው ነው ብለዋል።

ሽብርተኛው ህወሓት ለሶስተኛ ጊዜ የከፈተብንን ጦርነት በህዝብ ተሳትፎ ቀልብሰን ብልጽግናችንን ለማረጋገጥ ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ማለታቸውንም ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.