የግሸንን መስቀለኛ የተራራ ስፍራ የጎብኚዎች መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 7 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የግሸንን መስቀለኛ የተራራ ስፍራ የጎብኚዎች ተመራጭ መዳረሻ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የደቡብ ወሎ ዞን አስታወቀ።
አመታዊውን የግሸን ደብረ ከርቤ በዓል ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ስራ መሰራቱን የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳዳሪ አብዱ ሁሴን ተናግረዋል።
በዓሉ ባለፉት ሁለት አመታት ከኮሮና እና ተፈጥሮ ከነበረው የፀጥታ መደፍረስ ጋር በተያያዘ ድምቀት አለመከበሩንም አስታውሰዋል።
የዘንድሮውን በዓል ለማክበር ከተለያዮ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚጓዙ ምዕመናንና ጎብኚዎች፥ አካባቢው ፍፁም ሰላም መሆኑን አውቀው በስፍራው በመገኘት እንዲያከብሩም ጠይቀዋል።
ዞኑ ከአዲስ አበባ ጀምሮ ተጓዦች ችግር እንዳይገጥማቸው እየሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ከደላንታ መገንጠያ እስከ ግሸን ደብረ ከርቤ ድረስ ያለውን የጠጠር መንገድ የመጥረግና የማስተካከል ተግባር እየተከናወነ ሲሆን በጥቂት ቀናት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ብለዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ግማደ መስቀል መገኛ የሆነው የግሸን ደብረ ከርቤ አምባን የጎብኚዎች ተመራጭ መዳረሻ በማድረግ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዮኔስኮ) በቅርስነት ለማስመዝገብ የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ መጠናቀቁንም አስረድተዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን አባተ በበኩላቸው፥ በየአመቱ በመስከረም 21 ቀን የሚከበረውን የግሸን ደብረ ከርቤን በዓል ጨምሮ ከመስቀል እስከ ግሸን የዓለም ቱሪዝም ቀንን በስፍራው ለማክበር ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።
በዘንድሮው በዓል ላይ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ምዕመናን ይገኛሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፥ በአምባው ላይም የስልክ፣ መብራትና ውሃ አገልግሎት ሳይቆራረጥ ለማድረስ ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም አንስተዋል።
በኢሳያስ ገላው