የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል መስከረም 21 እና መስከረም 22 ቀን ይከበራል
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 10 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል መስከረም 21 እና መስከረም 22 ቀን እንደሚከበር የኦሮሞ አባ ገዳዎች አስታወቁ።
በዓሉ መስከረም 21 ቀን ሆራ ፊንፊኔ በአዲስ አበባ እንዲሁም መስከረም 22 ቀን ደግሞ በቢሾፍቱ ሆራ ሃርሰዴ እንደሚከበርም ነው የገለጹት።
የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት የኢሬቻ በዓል አከባበርን አስመልከተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም የኢሬቻ በዓል በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአባ ገዳዎች ህብረት ሊቀመንበር አባ ገዳ ጂሎ ማንዶ የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል የኦሮሞን ህዝብ ባህል እና እሴት ተከትሎ እንዲከበር ሁሉም ሃላፊነቱን እንዲወጣ ገልጸዋል።
የአባ ገዳዎች ህብረት ፀኃፊ እና የቱለማ አባገዳ ጎበና ሆላ የኢሬቻ በዓል የቱሪዝም መስህብ ሆኖ እንዲቀጥል ለክብረ በዓሉ የሚመጡ ሰዎች የባህል አልባሳት እና መዋቢያ ጌጦችን በመልበስ እንዲያደምቁ ጥሪ ማቅረባቸውን ኦ ቢ ኤን ዘግቧል።