አንድነትን የሚያጠናክሩ እሴቶችን ለትውልድ ማሸጋገር የሁላችንም ኃላፊነት ነው – አቶ አሻድሊ ሀሰን
አዲስ አበባ፣ መስከረም 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አንድነትን የሚያጠናክሩ ባህላዊ እሴቶችን በአግባቡ ጠብቆ ለትውልድ ማሸጋገር የሁላችንም ኃላፊነት ነው ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ፡፡
የቦሮ ሽናሻ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ጋሪ ዎሮ” በዓል “ጋሪ ዎሮ ለይቅርታ፣ ለአብሮነታችንና ለሰላማችን” በሚል መሪ ሐሳብ በአሶሳ ከተማ እየተከበረ ነው፡፡
በበዓሉ ላይ÷ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን አሻድሊ ሀሰን፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጌታሁን አብዲሳን ጨምሮ የፌዴራል እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
አቶ አሻድሊ ሀሰን በበዓሉ አከባበር ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ክልሉ የበርካታ ተፈጥሯዊና ባህላዊ ጸጋዎች ባለቤት መሆኑን ጠቅዋል፡፡
እነዚህን ጠቃሚ ጸጋዎች የሕዝቡን ሕይወት ሊቀይሩ በሚችሉበት ሁኔታ መጠቀም እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
የቦሮ ሽናሻ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ጋሪ ዎሮ” አዲስ ተስፋ የሚበሠርበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ባህላዊ እሴቶችን ለማልማት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ አለምነሽ ይባስ እንደገለጹት÷ የቦሮ ሽናሻ ብሔረሰብ “ጋሪ ዎሮ” በዓል ለሕዝቦች አብሮነትና ወዳጅነት ተምሳሌት የሚሆን ባህላዊ እሴት በመሆኑ በአግባቡ ለትውልድ ማሸጋገር ይገባል፡፡