አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሸገር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን ሥራ አስጀመሩ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ሸገር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን በዛሬው ዕለት ሥራ አስጀምረዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስን ጨምሮ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ሰዓዳ አብዱረህማን፣ የሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር)፣ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም አባ ገዳዎች ተገኝተዋል፡፡
አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በክልሉ የትምህርት ጥራትን እና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
ለዚህም ኢንስቲትዩቱ በትምህርት ዘርፉ የሚስተዋሉ የተደራሽነት ውስንነቶችን በመፍታት ረገድ ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖረው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ሸገር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዘመኑን የዋጀ፣ ብቁ እና በክህሎት የታነጸ ተወዳዳሪ ዜጋ ማፍራት ያስችላል ብለዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ በዛሬው ዕለት ተማሪዎችን በመቀበል በይፋ ሥራ መጀመሩንም ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡