የህግ የበላይነትንና የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ስርዓቱን የማስጠበቅ መደበኛ ስራ ይቀጥል- ጠቅላይ አቃቤ ህግ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የህግ የበላይነትንና የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ስርዓቱን የማስጠበቅ መደበኛ ስራ እንደሚቀጥል ገለፀ።
የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በተመለከተ እና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫውም የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መንግስት የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ያስቀመጠውን አቅጣጫ የሚከተል መሆኑን አስታውቀዋል።
ሆኖም ግን ተቋሙ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት በተለይም ከፖሊስና ከፍርድ ቤቶች ጋር በተቀናጀ መልኩ የሚሰራ በመሆኑ እና የፌደራል ፍርድ ቤቶች ከመጋቢት 10 እስከ 24 ቀን 2012 ዓ.ም በከፊል ዝግ ሆነው እንደሚቆዩ በተቋሙ የተሰጠውን ውሳኔ ግምት ውስጥ በማስገባት የተለያዩ ውሳኔዎችን ማስቀመጡን ገልፀዋል።
በዚህ መሰረት የህግ የበላይነትን እና የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ስርዓቱን ከማስጠበቅ አንጻር ከዚህ ቀደም ሲያከናውን የነበረውን መደበኛ ስራ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የምርመራ ሥራ፣ ጥቆማ እና የተጠርጣሪዎችን መዛግብት የማጣራት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉም ነው ያሉት።
በተጨማሪም ትላልቅ ሀገራዊ ወንጀሎችን ለመከላከል የሚደረጉ ተግባራት ተጠናክሮ ይቀጥላሉ ብሏል የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በመግለጫው።
እንዲሁም በሁሉም የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ምድብ ፅህፈት ቤቶች የሚሰጡ አገልግሎቶችና ቅሬታዎች በሙሉ እንደሚስተናገዱ በመጥቀስ፥ በአጠቃላይ ከፍርድ ቤቶች ችሎት በዘለለ ሁሉም ሥራዎች በተገቢው ሁኔታ እየተሰራ ይቀጥላልም ነው ያለው።
የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በተጠርጣሪ ማቆያዎች (ፖሊስ ጣቢያዎች ) የሚደረገው ዕለታዊ ግንኙቶች እንዲሁም ተጠርጣሪዎችን የሚያነጋግሩ ዐቃቤ ህጎች በጥንቃቄ እና ቫይረሱን ለመከላከል በተቀመጠው አግባብ መሰረት የሚፈጸሙ መሆኑንም ጠቅሷል።