ገደኛው ቪክቶር ዮከሬሽ…
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ቪክቶር ኢናር ዮከሬሽ የተወለደው በአውሮፓዊቷ ሀገር ስዊዲን በፈረንጆቹ 1998 ነው፡፡
በፈረንጆቹ 2015 በሀገሩ ክለብ ብሮማፖጅካርና የመጀመሪያ ጨዋታውን በማድረግ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ህይወትን የጀመረው ቪክቶር÷ በብራይተን፣ ኮቨንተሪ ሲቲ እና ስዋንሲ ሲቲ በመሳሰሉ የእንግሊዝ ክለቦች ያልተሳካ ጊዜን አሳልፏል፡፡
በውጣ ውረድ የተሞላው የቪክቶር ዮከሬሽ የእግር ኳስ ህይወት ተጫዋቹን ተስፋ ከማስቆረጥ ይልቅ ይበልጥ እያስተማረውና እያጠነከረው ሲሄድ ተስተውሏል፡፡
በፈረንጆቹ 2023 የፖርቹጋሉ ስፖርቲንግ ሊዝበንን የክለቡ ክበረ ወሰን በሆነ ዋጋ ተፈራርሞ የተቀላቀለው ቭክቶር÷ በ2020 የጀመረውን የሩብን አሞሪም ስፖርቲንግን ለስኬት በማድረስ በማድረስ ረገድ ከፍተኛውን ሚና ተጫውቷል፡፡
ቪክቶር በፈረመበት የመጀመሪያው ዓመት ስፖርቲንግ ሊዝበን ከረጅም ዓመታት በኋላ የፖርቹጋል ፕሪሜራ ሊጋ አሸናፊ እንዲሆን አስችሎታል፡፡
በዚህም በፈረንጆቹ 2022/2023 የውድድር ዓመት ስፖርቲንግ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ ሲሆን÷ ቪክቶርን ወደ ቡድኑ መቀላቀሉን ተከትሎ በፈረመበት የመጀመሪያው ዓመት ክለቡ ከ19 ዓመታት በኋላ የፖርቹጋል ፕሪሜራ ሊጋ አሸናፊ መሆን ችሏል፡፡
በቀጣዩ ዓመት 2024/25 የውድድር ዓመትም የአሞሪሙ ቡድን ስፖርቲንግ ሊዝበን ከዋና ተቀናቃኞቹ ፖርቶ እና ቤኔፊካ በመብለጥ የፕሪሜራ ሊጋው አሸናፊ እንዲሆን ቪክቶር ዮከሬሽ የአንበሳውን ደርሻ ተጫውቷል፡፡
በውድድር ዘመኑ የሊጋው ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ያጠናቀቀው ቪክቶር÷ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ብቻም ሳይሆን የገርድ ሙለር አሸናፊ በመሆን ስፖርቲንግን ተሰናብቷል፡፡
ከዛም በመቀጠል ለተከታታይ ዓመታት ሁለተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ማሳካት ያልቻለውና በብዙዎች ኔትፍሊክስ ተከታታይ ፊልም በሚል ሲሾፍበት የነበረው አርሰናል በፈረንጆቹ 2024 ቪክቶር ዮከሬሼን ከከፍተኛ የዝውውር ውዝግብ በኋላ ማስፈረም ችሏል፡፡
ከብዙ መስዋዕትነት በኋላ ሰሜን ለንደን የደረሰው ቪክቶር እንደተጠበቀው ውጤታማ የሆነ የውድድር ዓመት ጅማሮ ባለማድረጉ በእግር ኳስ ተመልካቾች ዘንድ አርሰናል በዝውውሩ መክሰሩ ሲነገር ቆይቷል፡፡
ሆኖም ግን ቪክቶር እግሩ እንግሊዝ በረገጠበት የመጀመሪያው ዓመት 22 ዓመታት ከሊግ ዋንጫ ርቆ የቆየው አርሰናል የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ አሸናፊ መሆን ችሏል፡፡
ቪክቶር ኢናር ዮከሬሽ በአርሰናል ቆይታው 35 የፕሪሚየር ልግ ጨዋታዎች ላይ በመሳተፍ 14 ግቦችን አስቆጥሯል።
በቪክቶር እና ጓደኞቹ እልህ አስጨራሽ ትግል የሊጉን ዋንጫ ያሳካው አርሰናል በክለቡ የውድቀት ዓመታት ልባቸው ተሰብሮ የነበረው ደጋፊዎች ደስታቸውን በእንባ ታጅበው በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡
በአቤል ነዋይ