Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ በዘላቂነት ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ ነው -ኢ/ር አይሻ መሀመድ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 23 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል በየዓመቱ የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ በዘላቂነትና በአጭር ጊዜ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ እንደሚገኝ የመስኖና ቆላማ አከባቢዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ገለጹ።
 
በክልሉ የተከሰተውን የጎርፍ አደጋ ለመመልከትና ምላሽ ለመስጠት የመስኖና ቆላማ አከባቢዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድና ሌሎች የክልልና የፌዴራል የስራ ኃላፊዎች በጎርፍ የተጎዱ አከባቢዎችን ጎብኝተዋል።
 
ኢንጂነር አይሻ መሀመድ የጎርፍ አደጋው በኑዌርና አኝዋሃ ዞኖች መከሰቱንና በርካታ ነዋሪዎች ላይም ጉዳት ማድረሱን መመልከታቸውን ተናግረዋል።
 
በየዓመቱ የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ በአጭር ጊዜና በዘላቂነት ለመፍታት የሚመለከታቸውን የፌዴራል መስሪያ ቤቶችን በማስተባበር የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ አንስተዋል።
 
ሚኒስቴሩ በየዓመቱ የጎርፍ አደጋ የሚያስከትለውን ጉዳት ወደ ልማት ለመቀየር በጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
 
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው በክልሉ አስር ወረዳዎችና በጋምቤላ ከተማ የጎርፍ አደጋ መከሰቱን ገልፀው÷ በጎርፍ የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍና ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።
 
የክልሉ መንግስት 10 ሚሊየን ብር በጎርፍ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ማድረጉን የገለፁት አቶ ኡሞድ÷ ይሁን እንጂ በቂ እንዳልሆነና የፌደራል መንግሥትም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
 
የፌደራል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም ÷ ኮሚሽኑ በጋምቤላ ክልል በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ከአራት ጊዜ በላይ ለተጎጂዎች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል።
 
በቀጣይም የሚመለከታቸውን አካላት በማስተባበር ለተጎጂዎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማስረዳታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.