Fana: At a Speed of Life!

የኮሮና ወረርሽኝ በኢኮኖሚ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት በመለየት የሚቻለውን ለማድረግ መንግሥት እንቅስቃሴ ጀምሯል – ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮና ወረርሽኝ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ተጨባጭ ጉዳት ፈጥኖ በመለየት የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ መንግሥት እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፌስቡክ ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት የጤና ባለሙያዎችን አመስግነው፥ “ጀግኖቹ የጤና ባለሙያዎቻችን ሕዝብን ከስቃይ ለመታደግ አያሌ መሥዋዕትነት ከፍለዋል፤ በሁሉም የጦር ግንባሮች ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን ተሰልፈው ለድንበራችን መከበርና ለሉዓላዊነታችን መረጋገጥ ሕይወታቸውን ሰጥተዋል” ብለዋል።

”እኛ ጤና እንድንሆን ሁሉም ጤና ይሁን” በሚለው መርሕ መሠረት፣ ሀገርን እና ሕዝብን ወክለው በኢቦላ ወረርሽኝ ወቅት፣ ከ150 በላይ የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎቻችን ወደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በመጓዝ አፍሪካውያን ወንድሞቻችንን አገልግለው በድል መመለሳቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ መሆኑንም አንስተዋል።

ተደምረን የማንሻገረው ፈተና፣ ተባብረን የማናልፈው መከራ አይኖርም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን የመከላከል ዘመቻ፣ የጤና ባለሙያዎቻችን ግምባር ቀደም ተሰላፊ በመሆን እስከ አሁን ላከናወኑት አኩሪ ገድል በኢፌዴሪ መንግሥትና በራሳቸው ስም ምስጋና አቅርበዋል።

“ፈተናውን በድል መወጣት እስከሚቻል ድረስ መንግሥት ሁሉንም ኃይሎች አስተባብሮ ከእናንተና ከቤተሰቦቻችሁ ጎን እስከ መጨረሻው የሚሰለፍ መሆኑን አረጋግጥላችኋለሁ” ሲሉም ገልፀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.