የኬንያው ፕሬዚዳንት የሳይንስ ሙዚየምን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በዚህ ሳምንት የተመረቀውን የሳይንስ ሙዚየም ጎበኙ፡፡
በጉብኝቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ ሌሎችም የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ዛሬ አዲስ አበባ መግባታቸውን እና በሁለተዮሽ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር መወያየታቸው ይታወቃል፡፡
የሳይንስ ሙዚየሙ መስከረም 24 ቀን 2015 ዓ.ም በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ መከፈቱ ይታወሳል፡፡
ሙዚየሙ ሁለት ግዙፍ ሕንጻዎች ሲኖሩት በሰባት ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ነው፡፡
በሙዚየሙ ውስጥ ቋሚ እና ጊዜያዊ ዐውደ ርዕይ ማሳያዎች ያሉ ሲሆን÷ ሙዚየሙ ሳይንስ ጥበባዊ በሆነ መንገድ የሚገለጽበት ጥበብም ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሚታይበት ነው።
ከተፈጥሮ ስርዓት ጋር ተስማሚ ሆኖ የተገነባው ሙዚየሙ ከጸሐይ ብርሀን የኤኤሌክትሪክ ኃይል ያገኛል።
የሙዚየሙ ውጫዊ ክፍል የቀለበት እና የጉልላት ቅርጽ እንዲኖረው ተደርጎ ነው የተገነባው፡፡
በፀጋዬ ወንድወሰን