በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 11 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ስንዴ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በበጋ ወራት 11 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ስንዴ ለማልማት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ፡፡
የክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ኻሊፋ እንደተናገሩት፥ በክልሉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ለሚከናወነው የበጋ መስኖ ስንዴ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡
በበጋ ወራት 11 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ስንዴን ለማልማት መታቀዱን የገለጹት ሀላፊው፥ ለበጋ ስንዴ ልማት የተለዩ ማሳዎችን የማጽዳት እና የእርሻ ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
ለአርሶ-አደሩ የሚቀርብ 6 ሺህ ኩንታል የስንዴ ምርጥ ዘር ግዢ መፈጸሙን እና በቅርቡም ለአርሶ-አደሩ እንደሚሠራጭም ነው የተመለከተው፡፡
በክልሉ በ2014 የመኽር ምርት ዘመን 8 ሺህ 622 ሄክታር መሬት በስንዴ ዘር መሸፈኑን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ መላክታል፡፡