Fana: At a Speed of Life!

1 ሺህ 497ኛው የመውሊድ በዓል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተከበረ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 28 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 1 ሺህ 497ኛው የነቢዩ መሐመድ የልደት በዓል (መውሊድ) በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተከብሯል።

በዓሉ በጅማ ከተማ አንጋፋው መድረሰቱል ኸይርያ ውስጥ ተከብሯል።

ይህ ትምህርት ቤት የእስልምና ትምህርት እንዲስፋፋ ካደረጉ ተቋማት አንዱና በ1942 ዓ.ም የተመሰረተ ነው።

በክብረ በዓሉ ላይም የጅማ ከተማ ሙስሊም ማህበረሰብ የተገኘ ሲሆን ነብዩን የሚያወድሱ የተለያዩ ዝማሬዎችም በወጣቶች ቀርቧል።

በተመሳሳይ በዓሉ በልዩ ልዩ ስነስርዓቶች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ተከብሯል፡፡

አሶሳ ከተማ በሚገኘው አል- ሂላል  መስጅድ በዓሉ በተለያዩ  ነሽዳዎች፣ መንዙማና ሌሎች ስነስርዓቶች ተከብሯል፡፡

በተያያዘም በዓሉ በደቡብ ወሎ ዞን አልብኮ ወረዳ ጀማ ንጉስ መስጂድ በድምቀት ተከብሯል።

ዘረኝነት የሠውን ልጅ የምታረክስ ስትሆን ፍቅር፣ አንድነትና መተዛዘን ለግን ሠው ልጅ ለአኬራ መንገዱ የተሠጡት ምርኩዙ መሆናቸውን 6ኛው የጀማ ንጉስ መሥጂድ ካሊፋ ሀጅ ሙሀመድ ዑስማን ተናግረዋል።

የሠው ልጅ መነሻው አደምና ሀዋ ናቸው ሌላ የሠው ጠባይ ያለው ሠው ከመሀላችን የለም ያሉት ሀጅ ሙሀመድ፥ አኗኗራችንን እንጅ  ቋንቋችን፣ መልካችን፣ አለባበሣችን፣ የሠውነት ፀባያችንን አይቀይርም ብለዋል።

ወጣቱ ትውልድም የውጭውን ዓለም ከማማተር ይልቅ ሀገሩ ያላትን በመመርመር አባቶቹ በተከሉት ፍቅር መከባበርና አንድነት ላይ ሊቆም እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የእምነት አባቶች ስለ ሀገር ሠላም ስለ ሠው ልጆች መልካምነት ዱአ በማድረግ፥ ያጠፋን መገሰጽ፣ የተጣላን ማስታረቅ፣ የይቅርታ መንፈስን ለልጆች ማስተማር ይገባቸዋልም ነው ያሉት።

የጀማ ንጉስ መሥጂድ የመውሊድ በዓል በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረበት ታሪካዊ መሥጂድ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.