Fana: At a Speed of Life!

ዩኒቨርሲቲዎች የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል እያደረጉ ያሉትን ቅድመ ጥንቃቄ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 12 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ዩኒቨርሲቲዎች የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል እያደረጉ ያሉትን ቅድመ ጥንቃቄ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ፐሮፌሰር ሂሩት ወልደ ማርያምና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቱትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ ከ45 የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችና ምክትል ፕሬዚዳንቶች ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱም ዩኒቨርሲቲዎች ቫይረሱን ለመከላከል አስፈላጊውን ስራ በሙሉ እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ የተለያዩ የንጽህና መጠበቂያ ፈሳሾችን ለተማሪዎች ተደራሽ ማድረግ ፣ተማሪዎች ከግቢ እንዳይወጡ ማድረግ ፣ ተማሪዎችን የሚያሰባስቡ ጉዳዮችን መቀነስ(እንደ ፈተና መሰረዝ ፣እንደ ቤተመጻህፍት ያሉ ነገሮች) እና ካፌ ተጠጋግተው እንዳይቀመጡ ማድረግ ተጠቅሰዋል።

እንዲሁም ሌሎች ቴክኒካዊ ዝግጅቶችን በዩኒቨርሲቲ ጊቢ ውስጥ እያከናወኑ እንደሆነና ለዚህ መሳካት የሚረዳ ግብረ ሀይል የማቋቋም ስራ መሰራቱን ዩኒቨርሲቲዎች ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሯ በበኩላቸው ከአንድንድ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው የሄዱ ተማሪዎች ባሉበት እንዲቀመጡና ወደ ዩኒቨርሲቲው እንዲመለሱ ካልተነገራቸው በቀር መመለስ እንደሌለባቸው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ወደ ዩኒቨርስቲዎች ቅጥር ግቢ የሚገቡ የአስተዳደር ሰራተኞችና መምህራን ቁጥር መቀነስና አስፈላጊውን ክትትል ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

ቫይረሱ ወደ ዩኒቨርሲቲዎቹ ቢገባና ምልክቶቹ ቢታዩ እንኳን ከክልሎች ጋር በጋራ በመሆን አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማከናወን እንደሚገባቸው ተነግሯል፡፡

የቫይረሱን ምልክቶች የሚያሳዩ ካሉ ተማሪዎች ጥቆማ የሚሰጡባቸው ነጻ የስልክ መስመሮች በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች መዘጋጀታቸውንም ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደ ማርያም አንስተዋል፡፡

ዶክተር ኤባ አባታ በበኩላቸው መደረግ ያለባቸውን ቅድመ ዝግጅቶችና ጥንቃቄዎች በመረጃ የተደገፈ ጥናት አቅርበዋል፡፡

አሁን የተጀመሩ ስራዎችም አበረታች መሆናቸው እና ለመከላከል ስራው የሚያገልግሉ ስራዎችን በአፋጣኝ መከወን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም አሁን የተገኙትን ልምዶች በመውሰድ ቫይረሱ በዩኒቨርሲቲዎች እንዳይከት ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መሰራት እንዳለበትና ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት መሰራት እንዳለበት ተነግሯል፡፡

በዘቢብ ተክላይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.