Fana: At a Speed of Life!

የቡና ገለባ ከተበላሸ ለውዝ ጋር ቀላቅሎ የምግብ ዘይት ሲያመርት በተገኘ ተቋም ላይ እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ቀጨኔ አካባቢ የቡና ገለባ ከሻገተ ለውዝ ጋር በመቀላቀል የምግብ ዘይት ሲያመርት በተገኘ ተቋም ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ምግብ መድሃኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ምግብ መድሃኒት ቁጥጥር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ኤልያስ÷ ህገ ወጥ ምርቱ የደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች ባደረጉት መደበኛ ክትትል መሰረት የተያዘ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በተቋሙ ላይ ቅኝት ሲደረግም ዘይት ማምረቻው የጤና ብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት የሌለው፣ ለግብዓትነት የሚጠቀምባቸው ምርቶች ጥራታቸውና ደህንነታቸው ያልተጠበቀ እንዲሁም የንጽህና አጠባበቅ መስፈርቶችን ያላሟላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የቡና ገለባ ከተበላሸ ለውዝ ጋር በመቀላቀል የምግብ ዘይት ሲያመርት መገኘቱን ጠቁመው÷ ለዚህም ተቋሙ ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን አረጋግጠዋል፡፡
ድርጅቱ የተጠቀመባቸው ግብዓቶች ተገቢ ካለመሆናቸው በተጨማሪ በቀላሉ የሚበላሹና አፍላ ቶክሲን በመፍጠር ለተለያዩ የካንሰር በሽታ አጋላጭ እንደሆኑ መጥቀሳቸውንም ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ተቋሙ የተጠቀመባቸው ጥሬ እቃዎች እና ባዕድ ግብዓቶች በአግባቡ እንደሚወገዱና በጉዳዩ ላይ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.