Fana: At a Speed of Life!

የሰላም ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች በፖሊስ ሆስፒታል የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ጥረት ጎበኙ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 12 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ)  የሰላም ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች የኮቪድ-19 ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማበረታታት የፌዴራል ፖሊስ ሆስፒታል እና በኮልፌ ክፍለ ከተማ የሚገኘውን የፌደራል ፖሊስ የመኖሪያ ካምፕን ጎበኙ፡፡

ጉብኝቱ ሰሞኑን በሀገሪቱ የተከሰተውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል የፖሊስ ሰራዊቱ እራሱን ጠብቆ ህበረተሰቡንም ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ለመመልከት እና ለማበረታታት እንዲሁም የድጋፍ ፍላጎቶችን ለመለየት የተደረገ ነው፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ሆስፒታል ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ቡድን በማዋቀርና የድንገተኛ ክፍሎች በማዘጋጀትና አምቡላንሶችን በማመቻቸት ሊፈጠሩ ለሚችሉ ክስተቶች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እንደተደረገ በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

በፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋማትም ለፖሊስ ሰራዊቱ አስፈላጊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰራዎች እየተከናወኑ እና የንፅህና መጠበቂያ ግብአቶችን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋማት፣ በሆስፒታሉ  እንዲሁም መላው ሰራዊቱ በተሰማራባቸው አካባቢዎች ሁሉ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል አሳስበዋል፡፡

ሚኒስትሯ የፖሊስ ሰራዊት የሀገሩን ሰላም ለመጠበቅ ግምባር ቀደም ኃይል በመሆኑ ከዚህ ወረርሽኝ እራሱን ጠብቆ በሙሉ ጤንነት ወገኑን ከዚህ ሃገራዊ ስጋት የመከላከል ከፍተኛ ሃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

አክለውም ከዚህ ወረርሽኝ የፖሊስ ሰራዊቱ በበቂ ግንዛቤ እራሱን የመከላከል፣ ስለ በሽታው የጠራ መረጃ የማቅረብ እና ትምህርት የመስጠት ስራ እንዲሁም የሱፐርቪዥን ስራ ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

በጉብኝታቸው ማጠቃለያም እየተሰራ ላለው ስራ አቅም ይጨምር ዘንድ የአፍንጫና አፍ ጭምብል፣ የእጅ ጓንቶች እና ተውሳክ ማምከኛ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መበርከቱን ከሚኒስቴሩ ያኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.