Fana: At a Speed of Life!

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና አሰጣጥ በትምህርት ላይ እየመጣ ላለው ለውጥ ማሳያ ነው – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 2 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የመልቀቂያ ፈተና አሰጣጥ በትምህርት ላይ እየመጣ ላለው ለውጥ አንዱ ማሳያ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የመልቀቂያ ፈተና የመጀመሪያ ምዕራፍ መጠናቀቅን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ውስጥ ከገባችበት ጀምሮ በርካታ ተቋማዊ እና የፖሊሲ ሪፎርም እርምጃዎችን መውሰዷን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል።

ከእነዚህ የለውጥ እርምጃዎች መካከል አንዱ የትምህርት ዘርፍ ሪፎርም መሆኑን ጠቅሶ፥ ባለፉት ዓመታት ከተደራሽነት አንፃር መልካም ሥራዎች የተሠሩ ቢሆንም የትምህርት ጥራት በእጅጉ ተዳክሞ መቆየቱን አስታውሷል፡፡

መንግሥት የትምህርት ጥራትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ፓኬጆችን በመቅረፅ በርካታ የሪፎርም እርምጃዎች እየወሰደ ይገኛል ብሏል፡፡

ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል የምዘና ሥርዓትን ማሻሻል አንዱ ሲሆን፥ ይህንን ለማሳካት አንዱ ምእራፍ የሆነው የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የመልቀቂያ ፈተና በተለየ ሁኔታ በከፍተኛ ዝግጅትና ተቋማዊ ቅንጅት በመሰጠት ላይ ይገኛል ብሏል፡፡

የአሁኑ ፈተና አሰጣጥ ከዚህ በፊት በብልሹ አሠራር፣ በስርቆት እና በማጭበርበር ይደረግ የነበረውን የፈተና ሂደት በማስቀረት ሁሉም ተማሪ እኩል የሚመዘንበት ዕድል እንዲፈጥር ታሳቢ ያደረገ ነው መሆኑንም ጠቅሷል፡፡

በዚህ በ2014 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የመልቀቂያ ፈተና ከኩረጃና ከስርቆት እንዲሁም ከሌሎች ብልሹ አሠራር የጸዳ እንዲሆን መንግሥት በቢሊየን የሚቆጠር በጀት በመመደብ ወደ አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ተማሪዎችና ፈታኝ መምህራንን በማጓጓዝ፣ እንዲሁም አስተባባሪዎችን በመመደብ በ160 ማዕከላት ፈተናው በሰላም እና ከጸጥታ ሥጋት ነፃ በሆነ መልኩ እንዲፈፀም በማድረግ ለትምህርት ጥራት ያለውን ቁርጠኝነት አሳይቷልም ነው ያለው አገልግሎቱ፡፡

እስከ አሁን ባለው አፈጻጸም የመጀመሪያ ዙር የፈተና አሰጣጡ ከጥቂት ችግሮች በስተቀር በተሳካ ሁኔታ
መከናወኑን ያነሳው መግለጫው፥ በሀገራችን ታሪክ ሚሊየን ተማሪዎችን በተወሰኑ ማዕከላት ሰብስቦ የመፈተን ልምድ የአሁኑ የመጀመሪያ መሆኑንም አውስቷል።

በትምህርት አመራሩ ቁርጠኝነት፣ በተፈጠረው ተቋማዊ ቅንጅት፣ በጸጥታ አካላት ትጋት፣ በመምህራንና በሌሎች የትምህርት ዘርፉ ባለድርሻ አካላት የዓላማና የተግባር አንድነት፣ የፈተናው ሂደት በተረጋጋና በተፈለገው ሁኔታ ሊቀጥል መቻሉንም ጠቅሷል።

አልፎ አልፎ ችግሮች በሚያጋጥሙበት ወቅት እንኳን ማኅበረሰቡ መክሮና ገሥጾ ችግሮች እንዲቀረፉ ማድረጉን በመጥቀስም፥ ልጆቹን በማረጋጋትና አስፈላጊውን ሁሉ ትብብር በማድረግ ለትምህርት ጥራት ያለውን ድጋፍና ቀናነት መግለጹንም አመላክቷል።

በዚህም የሕዝብ ቅቡልነት ያለው ማንኛውም ዕቅድና ሥራ ሁልጊዜም የሚሳካ መሆኑን ለሌሎች የሪፎርም ሥራዎች ጭምር ትምህርት እንደተወሰደበት አንስቷል።

በዚህ አጋጣሚ ልጆቹን በማበረታታት፣ ተፈታኞቹና ፈታኝ መምህራን ወደየማዕከላቱ ሲገቡ አቀባበል በማድረግ፣ ችግሮች ሲፈጠሩ ተማሪዎቹን በማረጋጋት፣ ሲያጠፉም በመምከርና በመገሠጽ ሂደቱ ሰላማዊና የተረጋጋ እንዲሆን ላደረጉ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና መላው ማኅበረሰብ፣ ፈታኝ መምህራን፣ የጸጥታ አካላትና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች ላደረጉት አስተዋጽዖ ምስጋናውን አቅርቧል።

በቀጣይ ሳምንት የሚሰጠው ሁለተኛው ምዕራፍ ፈተና በተሻለ ሁኔታ እንዲከናወን ሁሉም የጀመረውን ጥረት እንዲያጠናክርም ጥሪውን አቅርቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.