40 ኤፍ1 ቦምብ እና 15 ክላሽንኮቭ መሳሪያ ተያዘ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ዞን መተማ ወረዳ በማጠቢያ ንዑስ ወረዳ ጉባይ ቀበሌ ለሽብር ተግባር ሊውል የነበረ 40 ኤፍ1 ቦምብ መያዙን ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የመተማ ወረዳ ፖሊስ የታክቲክ ምርመራ ክፍል ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር ቸኮል ወርቄ እንደገለጹት÷ የቅማንት ኮሚቴ ከአሸባሪው ህወሓት ጋር በመሆን ለሽብር ተግባር ሊያውሉት የነበረ 40 ኤፍ1 ቦምብ ከሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
ቦምቡ በሕዝብ ጥቆማና በጸጥታ ኃይሉ ክትትል መያዙን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በተለያዩ ተቋማት እና ሰዎች በሚሰበሰቡበት አካባቢ በማፈንዳት በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ ታስቦ እንደነበር በምርመራ ማረጋገጣቸውንም ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል መነሻውን ጋምቤላ ያደረገ ኮድ 3 አዲስ አበባ 50799 አይሱዝ ተሽከርካሪ 15 ክላሽንኮቭ መሣሪያዎችን በድብቅ ጭኖ ወደ ምሥራቅ ጎጃም መርጦ ለማሪያም ሲጎዝ በጸጥታ አካላት በአዲስ አበባ ከተማ መያዙን ለመረጃው ቅርበት ያላቸዉ ታማኝ ምንጮች አረጋገጥዋል።
ይህንን ድብቅ እንቅስቅሴ ሲከታተሉ የነበሩ የመረጃና ደኀንነት አካላት ለአዲስ አበባ ፖሊስ ጥቆማ በመስጠት 15 የክላሽንኮቭ መሣሪያዎች ከሁለት አዘዋዋሪዎች ጋር አዲስ አበባ ከተማ ላይ እጅ ከፈንጅ ተይዘዋል።