አቶ ዛዲግ አብረሃ ከደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይና ዓለምአቀፍ ትብብር ሚኒስትር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አስተባባሪ ሚኒስትር ዛዲግ አብረሃ ከደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይና ዓለምአቀፍ ትብብር ሚኒስትር ማይክ አይህ ዴንጋ ጋር ተወያይተዋል፡፡
የትብብር ሚኒስትሩ የአረንዴ ዲፕሎማሲን በጎረቤት አገራት ለማጠናከር ወደ ደቡብ ሱዳን ጁባ ያቀኑ ሲሆን ከዚሁ ስራ ጎን ለጎንም ከተለያዩ የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
አቶ ዛዲግ ከደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይና ዓለምአቀፍ ትብብር ሚኒስትር ጋር በደቡብ ሱዳን ጁባ የተወያዩ ሲሆን በውይይታቸውም ደቡብ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው ብለዋል ።
አቶ ዛዲግ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ዲፕሎማሲ በማጠናከር በበርካታ ጉዳዮች ላይ መንግስት በቅርበት እንደሚሰራ ጠቁመው በሁለቱ ሀገራት መካከል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር በሁሉም መስኮች ትብብሮችን ማስፋት ይገባልም ብለዋል ።
በተመሳሳይ÷ አቶ ዛዲግ ከደቡብ ሱዳን የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትር አልቢኖ ቦል ጋር ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ በደቡብ ሱዳን እንዲስፋፋ በአካባቢ እና በተፈጥሮ ጥበቃ ስራዎች እንደሚጠናከርም አቶ ዛዲግ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃላቀባይ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ።