በጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የተመራ ልዑክ የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች የፖሊስ ሥራን ጎበኘ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 4 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የተመራ የልዑካን ቡድን የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች በአቡዳቢ የፖሊስ ሥራን ጎብኝቷል፡፡
የልዑካን ቡድኑ ዱባይ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ በተባበሩት ዓረብ ኢሚሬትስ ሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢንስፔክተር ጀነራል እና የወቅቱ የዓለም አቀፍ የፖሊስ ተቋም ፕሬዚዳንት ሜጀር ጀነራል አህመድ ናሲር አል-ረኢሲ አቀባብል አድርገውለታል፡፡
ልዑካኑ ከሜጀር ጀነራል አህመድ ናሲር አል-ረኢሲ ጋር የሁለቱን ሀገራት የፖሊስ አቅም ለማጠናከ ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር በኢንተርፖል ቨርቹዋል አካዳሚ የአቅም ግንባታ ሥልጠና የሚሰጥበትን ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡
ድንበር ተሻጋሪ የወንጀል ጉዳዮችን በተለይ የሀገር ሀብት ዘርፈው ወደ ውጭ ሀገር የሚያሸሹትን በጋራ ለመከላከልና መቆጣጠርበሚቻልበት ሁኔታ ላይም ውይይት አድርገዋል፡፡
እንዲሁም በቀጣይ በሁለትዮሽ ግንኙነትና ትብብር የሁለቱን ሀገራት የፖሊስ ተቋማት ስትራቴጂካዊ አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ መወያየታቸው ነው የተገለጸው፡፡
በጉዳዩ ላይ በጋራ ለመስራትም የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ እንደሚፈራረሙና ይህንኑን ተግባራዊ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አንድ ቡድን በቅርቡ ወደ አቡዳቢ እንደሚላክ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ሜጀር ጀነራል አህመድ ናሲር አል-ረኢሲ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሽብርተኝነትንና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል ከዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም ጋር በመተባበር እየሰራ ያለውን ተግባር አድንቀዋል።
ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጋር የተጀመረውን የቴክኖሎጂ አቅም የበለጠ ለማጠናከር እና በትብብር ለማስራት ቃል መግባታቸውን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡
ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በበኩላቸው÷የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀልን አስቀድሞ ለመከላከልና ወንጀል ተፈፅሞ ሲገኝ በብቃት መርምሮ ተጠርጣሪዎችን ለሕግ ለማቅረብ የሚያስችል የቴክኖሎጂ ሽግግር እያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በቅርቡ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ ከተማ በሚካሄደው 24ኛው የምሥራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት ጉባኤ ላይ እንዲገኙ የጋበዙ ሲሆን÷ ሜጀር ጀነራሉም ግብዣቸውን ተቀብለው በጉባኤው ላይ እንደሚገኙ ቃል ገብተዋል።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሴይፍ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋርም በአቡዳቢ ተገናኝተው በተለያዩ ጉዳች ላይ መክረዋል፡፡