አቶ አህመድ ሺዴ ከኮርፖሬት ካውንስል ፎር አፍሪካ ሃላፊዎች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ከኮርፖሬት ካውንስል ፎር አፍሪካ ሃላፊዎች ጋር በአጎዋ ነጻ የገበያ ዕድል ተጠቃሚነት ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
ከኮርፖሬት ካውንስል ፎር አፍሪካ በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ የሚሰራ የንግድ ፎረም ተቋም ነው።
በዓለም ባንክ፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅት ዓመታዊ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገኖች ስብሰባዎች ላይ ለመሳተፍ በአቶ አህመድ ሺዴ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በዋሺንግተን ዲሲ ከድርጅቱ ፕሬዚዳንትና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ጋር ተወያይቷል።
የውይይቱ ዋነኛ ትኩረት በአጎዋ ነጻ የገበያ ዕድል ተጠቃሚነት ዙሪያ ያተኮረ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የአጎዋ ነጻ የገበያ እድል ዕገዳው ዋና ተጠቂዎች ሕጻናትና ሴቶች እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መሆናቸው ተነስቷል።
ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን በመንግስት በኩል ቁርጠኝነት መኖሩን እንዲሁም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ዙሪያ ስለተመዘገቡ ውጤቶች፣ ለአጎዋ የገበያ እድል መመለስ ከተቀመጡ ቅድመ-ሁኔታዎች አንጻር ስለታዩ መሻሻሎች ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
የካውንሰሉ ፕሬዚዳንት ፍሎሪ ሊዘር በበኩላቸው÷ የግል ዘርፍ መር ኢኮኖሚን ለመገንባት እየተደረገ ስላለው ጥረት በቂ ግንዛቤ መጨበጣቸውን ገልጸዋል።
በእነዚህና መሰል ጉዳዮች ላይ መንግስት ለሚያደርገው ጥረት የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል።