በክልሉ የሥራ ዕድል ፈጠራን በማሳደግ የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል እየተሠራ መሆኑን አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ተናገሩ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው በጀት ዓመት በሶማሌ ክልል የሥራ ዕድል ፈጠራ ፕሮግራሞች ከእንስሳት ሀብት ልማት እና ከግብርና ልማት ዘርፎች ጋር በማቀናጀት እንደሚተገበሩ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ ተናገሩ፡፡
“አዲስ እሳቤ ለዘላቂ ጉዞ” በሚል መሪ ሐሳብ የሥራና የክህሎት ሚኒስቴር ለክልል፣ ለዞንና ከተማ አስተዳደር አመራሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እና በተቋሙ የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ በጅግጅጋ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡
አቶ ሙስጠፌ መሀመድ በመድረኩ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር÷ በክልሉ በገጠርና በከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራ በማሳደግ የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል።
ባለድርሻ አካለትም ዕቅዱን እውን ለማድረግ በተጠናከረ ሁኔታ ሊሠሩ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ነቢያ መሀመድ በበኩላቸው÷ መንግሥት የሀገሪቱን የሥራና ክህሎት ዘርፍ ለማሳደግ የተለያዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ቀርፆ ተግባራዊ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
በዘርፉ የተቀመጡ ዕቅዶችን እውን ለማድረግ አመራሮችና ባለሙያዎች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡