ኮርፖሬሽኑ ኢትዮጵያን ከ5 ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎች አንዷ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፊታችን ጥር 18 እና 19 ኢትዮጵያን ከ5 ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎች ተርታ በዘላቂነት በመሬት ይዞታ ልማት ዘርፍ ለማሰለፍ ፎረም ሊካሄድ መሆኑ ተገለጸ፡፡
“ኢንቨስት ኦሪጅንስ” የተሰኘው ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ለማምጣት ያቀደው የመሬት ይዞታን የሚያለሙ ድርጅቶችና ባለሐብቶችን በመሳብ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የፌዴራል መሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሌንሳ መኮንን ፎረሙን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ÷ ተቋማቸው ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ስትራቴጂ ቀርጾ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተለያዩ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ ሀገራት የሚዘጋጁ ፎረሞች ላይ በመሳተፍ ልምድና ተሞክሮ መወሰዳቸውንም ነው የተናገሩት።
በመኖሪያ ቤቶች፣ ጤና፣ ሆቴል፣ ትምህርትና አይ ሲ ቲ ዘርፎች ልማት ላይ የተለያዩ ጥራት ያላቸው ኢንቨስትመንቶች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዲሳቡ ለማድረግ እየተሰራ ነውም ተብሏል።
“ኢንቨስት ኦሪጅንስ” የተሰኘ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ በአካል 250 በበይነ መረብ 500 በድምሩ 750 የሀገር ውስጥና የውጭ ተቋማት፣ ባለሐብቶችና የዘርፉ ተዋናዮች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡