Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት የኮሮና ስርጭትን ለመቆጣጠር የተሳፋሪውን ቁጥር ቀነሰ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 14 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት ከዛሬ ጀምሮ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር የተሳፋሪውን ቁጥር መቀነሱን አስታወቀ።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ እርምጃው የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ያለመ መሆኑን አስታውቀዋል።

አያይዘውም ህብረተሰቡ የትራንስፖርት ጥግግት መጠንን በመቀነስ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ስንታየሁ ወልደሚካኤል በበኩላቸው፥ ኮርፖሬሽኑ ከዚህ ቀደም ይደረጉ በነበሩ ምልልሶች በቀን ከ120 ሺህ በላይ ለሆኑ ሰዎች አገልግሎት ይሰጥ ነበር ብለዋል።

ከዛሬ ጀምሮ የተሳፋሪዎችን ጥግግት በመቀነስ በቀን ከ48 እስከ 50 ሺህ ለሚደርሱ ሰዎች ብቻ አገልግሎት እንዲሰጥ መወሰኑንም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

በባቡር ሰልፍ ወቅት የአንድ ሜትር ርቀትን ለመጠበቅ የሚያስችል ምልክትም በወረፋ መጠበቂያ ቦታዎች ተደርጓልም ነው ያሉት።

ይህንኑ የእርስ በርስ መተፋፈግ ለመቀነስ ባቡር ውስጥም የወንበር ላይ ርቀት ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል።

የቅድመ ጥንቃቄ ስራው ሁሉም ተሳፋሪዎች ወደ ባቡር ከመግባታቸው በፊት ሰልፍ ሲይዙ እጃቸውን አልኮል እንዲቀቡ በማድረግ እንዲሁም ከወረዱ በኋላ ሌሎች ተሳፋሪዎች ከመግባታቸው በፊት ባቡር ውስጥ የኬሚካል ርጭት የማከናወን ስራ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።

በሶዶ ለማ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.