የስራ ባልደረቦቹን የይለፍ ቃል በመጠቀም ከ7 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ ወደ ሌላ ግለሰብ ያስተላለፈው የባንክ ሰራተኛ ላይ ክስ ተመሰረተ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 18 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ የስራ ባልደረቦቹን የይለፍ ቃል በመጠቀም ከ7 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ ከሁለት የባንኩ ደንበኞች አካውንት ከፍቃዳቸው እና ከዕውቅናቸው ውጭ ወደ ሌላ ግለሰብ ያስተላለፈው የአቢሲኒያ ባንክ ሰራተኛ ላይ ክስ መሰረተበት፡፡
የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያመላክተው አዲሱ ብርሀኑ የተባለው አንደኛ ተከሳሽ በአቢሲኒያ ባንክ የአስኮ ንዑስ ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት መኮንን ሆኖ ሲሰራ ለራሱ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ተከሳሽ የሁለት ጓደኞቹን የይለፍ ቃል በመጠቀም መስከረም 6 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 7፡50 ሰዓት ሲሆን የቅርንጫፍ ባንኩ ሰራተኞች ለምሳ በወጡበት ሰዓት የተሰጠውን ኃላፊነት ያለአግባብ በመገልገል፤ የባንኩ የአያት ባቡር ቅርንጫፍ ደንበኛ ከሆኑት ከወይዘሮ ተቋመች ወ/ጊዎርጊስ ሂሳብ ቁጥር ላይ 3,251,000 (ሶስት ሚሊየን ሁለት መቶ ሃምሳ አንድ ሺህ) ብር ቀንሶ ወደ ሌላ የባንኩ ደንበኛ ለሆነው ወደ አቶ አበበ ሙላቱ ሂሳብ ቁጥር አስተላልፏል።
እንዲሁም መስከረም 7 ቀን 2015 ዓ.ም ከጠዋቱ 1፡41 ሰዓት ሲሆን ጠዋት ማንም ሰራተኛ ስራ ሳይገባ ቀድሞ በመግባት የባንኩ የለገሀር ቅርንጫፍ ደንበኛ ከሆኑት ከወይዘሮ ፍሬወይኒ አባይ ሂሳብ ቁጥር ላይ 4,100,000 (አራት ሚሊየን አንድ መቶ ሺህ) ብር ቀንሶ ወደ ሌላ የባንኩ ደንበኛ ለሆነው ወደ አቶ ሳሚ ጌታቸው ሂሳብ ቁጥር ማስተላለፉ ተጠቅሷል።
በድምሩ 7,351,000 (ሰባት ሚሊየን ሶስት መቶ ሃምሳ አንድ ሺህ) ብር ከሂሳብ ባለቤቶቹ ፈቃድና እውቅና ዉጪ የሁለቱን የስራ ባልደረቦቹን የይለፍ ቃል በመጠቀም በማስተላለፍና ግብይቱን በማጽደቅ ጉዳት ማድረሱ በክስ መዝገቡ ተጠቅሷል።
የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9(2) በመተላለፍ በፈፀመዉ ስልጣንን አላግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ተከሷል።
በተያያዘም ዐቃቤ ህግ በክስ መዝገቡ ላይ ሁለተኛ ተከሳሽ ገመቹ ታከለ የባንኩ ቢዝነስ ኦፊሰር እንዲሁም ሶስተኛ ተከሳሽ ምንአለሸዋ መንግስቱ የባንኩ ኦፕሬሽን ኦፊሰር የሆኑት ተከሳሾች እራሳቸው ብቻ ሊይዙትና ሊጠብቁት የሚገባውን ኮድ ማወቅ ለማይገባው ሰው በቸልተኝነት እንዲያውቀው በማድረጋቸው በፈፀሙት የህዝባዊ ድርጅት ስራን በማያመች አኳኋን መምራት ወንጀል ተከሰዋል፡፡
ዐቃቤ ህግም የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን በማጠናቀር በመሰረተው ክስ ላይ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ለህዳር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ተከሳሾች የክስ መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡