Fana: At a Speed of Life!

አቶ እርስቱ ይርዳው በጉራጌ ዞን ማረቆ ወረዳ በኩታ ገጠም እየለማ ያለ የስንዴ ሰብል እየጎበኙ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 19 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በጉራጌ ዞን በማረቆ ወረዳ በዘንድሮው የመኸር አዝመራ በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ እየለማ ያለ የስንዴ ማሳን እየጎበኙ ነው።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት ከዚህ ቀደም በወረዳው በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ምክንያት በአርሶ አደሩ የግብርና ስራ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በባህላዊ እርቅ መፍታት በመቻሉ አሁን እየታየ ያለውን ሰብል ማልማት መቻሉ በሀገራዊ ምርት ላይ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሆነ ገልጸዋል ።

በደቡብ ክልል በመኸር አዝመራ 175 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል የተሸፈነ ሲሆን 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

በርዕሰ መስተዳድሩ የተመራው ልዑክ በስልጤ ፣ በሀላባ እና በወላይታ ዞኖች በመኸር አዝመራ እየለማ ያለ ሰብል ይጎበኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከደቡብ ክልል 1 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ  መታቀዱን  ርእሰ መስተዳድር እርስቱ ይርዳው ተናግረዋል፡፡

 

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት  በስልጤ ዞን ሚቶ ወረዳ የለማውን ኩታገጠም የስንዴ ማሳ በጎበኙበት ወቅት ነው።

 

ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የታቀደው ስንዴ ከፍጆታ ምርት በተለየ ደረጃውንና ጥራቱን ጠብቆ እየለማ መሆኑንና ክልሉ በሰብል ምርት ያስቀመጠውን ግብ ማሳካት የሚያስችል መሆኑን ማየት መቻሉንም ገልጸዋል።

 

የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከድር በበኩላቸው ÷ዞኑ በዘንድሮ መኸር 67 ሺህ ሄክታር ማሳ በኩታ ገጠም ስንዴ ስብል ለማልማት አቅዶ ማሳካቱን ገልጸው በመኸር ከለማው ስንዴ  ደግሞ አንድ ሶስተኛውን  ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየሠራ መሆኑን አብራርተዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.