የመጀመሪያው የአፍሪካ ወጣቶች ጉባዔ በአዲስ አበበባ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 19 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ አዘጋጅነት ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች ጉባዔ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ በመካሔድ ላይ ይገኛል።
የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤና ፍልስፍና ለአዲሱ የአፍሪካ ትውልድ ማስተዋወቅና አብሮነትን ማጠናከር ዓላማው ባደረገውና ለሦስት ቀናት በሚቆየው በዚህ ጉባዔ ከ50 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ወጣት መሪዎች ተሳታፊ ናቸው።
በዓለም አቀፍ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ አፍሪካ እንደ አህጉር ያላት ሚና እንዲጠናከር ለወጣቶች ማሳየት እንዲሁም የጋራ ትስስርን ማጎልበት የጉባኤው ዓላማ መሆኑን ተገልጿል።
በጉባዔው የኢትዮጵያ የቀድሞ መሪዎች ልምዳቸውን እንደሚያካፍሉ የሚጠበቅ ሲሆን፥ የሁሉም ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች ሚኒስትሮች በክብር እንግድነት ይገኛሉ ተብሏል።
በአፍሪካ ትብብርና ወንድማማችነት ላይ ያተኮሩ የተለያዩ የምርምርና ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ነው የተባለው።
ከወጣቶቹ በተጨማሪ በሕይወት የሌሉ የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ታጋዮች ቤተሰቦች በጉባኤው ላይ የሚታደሙ ሲሆን፥ ለታጋዮቹ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አማካኝነት ሽልማት እንደሚበረከትላቸው የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡