በከባድ ሰው መግደል ወንጀል የተከሰሰው ግለሰብ በ21 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት ተቀጣ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዚገም ወረዳ በከባድ ሰው መግደል ወንጀል የተከሰሰው ግለሰብ በ21 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት ተቀጣ::
ተከሳሽ ወንድሜ አለሙ ሆን ብሎ ሰው ለመግደል በማሰብ ጳጉሜን 5 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 12 ሰዓት በዚገም ወረዳ አበራች ዛዝብል ቀበሌ ልዩ ስሙ ኬልማ እየተባለ በሚጠራው ስፍራ የሚስቱ የግል ልጅ የሆነችውን የ8 አመት ህፃን መቅደስ ገደፋውን በዱላ እና በጩቤ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ገድሏል፡፡
ከገደላት በኋላም ወላጅ እናቷን በማስገደድ እና በማስፈራራት አስክሬኑን ለሶስት ቀን በመኖሪያ ቤቱ ካቆየ በኋላ መስከረም 2 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 3 ሰዓት የሟችን እናት /ሚስቱን/ አስገድዶ አስክሬኑን አሸክሞ ወስዶ ኬልማ ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን መቅበሩ ተገልጿል፡፡
እስከ ጥቅምት 9 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስም ለማንም ሳይገልጽ ቆይቶ ተደርሶበት ከቀበረበት ቦታ መርቶ ያሳየ በመሆኑና በፈፀመው ከባድ ወንጀል በፖሊስ ተጣርቶ በዐቃቤ ሕግ ክስ ተመስርቶ የቀረበለትን ክስ የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወንጀሉን ድርጊት ሲመረምር ቆይቷል፡፡
በዚህም ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም በጓንጓ ወረዳ ፍርድ ቤት ባስቻለው ተዘዋዋሪ ችሎት ተከሳሽ ወንድሜ አለሙ በፈፀመው ወንጀል ተከሳሹን ያስተምራል ሌሎችንም ያስጠነቅቃል በማለት 21 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን የአዊ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡